ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሞጣ አራት የጸጥታ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በአማራ ክልል፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ አራት የመንግሥት አመራሮች ዛሬ ታህሳስ 21/2012 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ለኃላፊዎቹ በቁጥጥር ስር መዋል ምክንያት የሆነው ባለፈው ሳምንት በሞጣ ከተማ በሀይማኖት ተቋሞች ላይ ቃጠሎ መድረሱ እንዲሁም የተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ነው።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ ተስፋዬ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በሞጣ ከተማ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር ኃላፊዎቹ የሚሊሻና የፖሊስ አመራር አቀናጅተውና ኃይል አሰባስበው ነገሮችን መከላከል እየቻሉ ይህንን ማድረግ አልቻሉም ብለዋል።
''የጸጥታ አመራሮችና ኃላፊዎች እንደመሆናቸው በስራቸው የሚያስተዳድሯቸውን የሚሊሻና የፖሊስ አመራሩን አቀናጅተውና አደራጅተው ነገሮችን መከላከል የሚችሉበት እድል እያለ በቂና የተደራጀ አመራር ባለመስጠት ተጠርጥረው አራቱ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል።''
በቁጥጥር ስር ከዋሉት አመራሮች መካከል ሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የሚሊሻ አመራር መሆናቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ አክለዋል።
''ከሁለቱ የፖሊስ አመራሮች አንደኛው የጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊና ሁለተኛው የወንጀል መከላከል ኦፕሬሽን መሪ ናቸው። ከሚሊሻ አመራሮች ደግሞ በተመሳሳይ የጽህፈት ቤት ኃላፊና የስምሪት ክፍል ኃላፊ ናቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።''
የተደራጀ የፖሊስና የሚሊሻ ኃይል እያለ በከተማዋ የደረሰው የቤተ እምነቶች መቃጠልና በርካታ የንግድ ሱቆች መቃጠል መከላከል አለመቻል ተቀባይነት የለውም ብለዋል ኢንስፔክተር አያልነህ።
ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በከተማዋ በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
የነዚህ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ከምን ደረሰ? ያልናቸው ኢንስፔክተሩ የምርመራው ስራ በተደራጀና ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሠራ እንደሆነና የመጨረሻ ውጤቱ በሚመለከተው አካል በኩል ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በከተማዋ አሁን ላይ ስላለው ሁኔታ ሲናገሩ ደግሞ የዞንም ሆነ የክልል አመራሮች እስካሁን በከተማዋ እንደሚገኙና ነገሮች እየተረጋጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
''ማህበረሰቡ እስከ ትናንት ድረስ ከቃጠሎውና ሌሎች ውድመቶች ጋር ተያይዞ ቀርተው የነበሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በህብረት ወጥቶ የጽዳት ዘመቻ አድርጓል። ከተማዋም የተረጋጋችና ወደቀደመው እንቅስቃሴው ተመልሳለች ማለት ይቻላል'' ብለዋል።