የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዚዳንት ባለቤት በባለቤታቸው ግድያ ሙከራ ተከሰሱ

ሜሪ ሙባይዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዚዳንት ባለቤት ሜሪ ሙባይዋ በባለቤታቸው ግድያ ሙከራ ተከስሰዋል።

የሙስና ክስ ያለባቸው ሜሪ ሙባይዋ ሰኞ እለት ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ ክሱንም ውንጀላ ነው በማለት ክደውታል።

አቃቤ ህግጋት በበኩላቸው ባለቤታቸውን ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋን ደቡብ አፍሪካ ህክምና እያደረጉ በነበረበት ወቅት ሊገድሏቸው ሞክረዋል ብለዋል።

ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ሮበርት ሙጋቤ ከሁለት አመት በፊት ከስልጣናቸው ሲገረሰሱም ቁልፍ ሚናን ተጫውተዋል።

ጄኔራሉም ቢሆኑ ከስድስት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ ህክምና እንዳያገኙ "ከፍተኛ ጫና አድርጋብኛለች" በማለት ወንጅለዋታል።

ከዚህም በተጨማሪ በፕሪቶሪያ ሆስፒታል ውስጥ እየታከሙ በነበረበት ወቅትም ግሉኮሱን ነቅላዋለች ብለዋል።

ጄኔራሉ ለተጨማሪ ህክምና ቻይና ሄደውም ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ተመልሰዋል።

ሜሪ ሙባይዋ በቁጥጥር ስር የዋሉት በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እለት ሲሆን ዋስም ተከልክለዋል። ከግድያ ሙከራ በተጨማሪ 750ሺ ዶላር ገንዘብ ከማጭበርበርና በህገወጥ መንገድ በማዘዋወርም ተከሰዋል።

የቢቢሲ አፍሪካ ዘጋቢ አንድሪው ሃርዲንግ እንደሚለው ከበርቴዎቹ በግድያ ሙከራና በመመራረዝ ውንጀላዎች ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ከመምጣታቸው አንፃር ይህ ሁኔታ አዲስ ነገር አይደለም።