ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ጥቃት 22 ንጹሃን ዜጎች ተገደሉ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቤኒ ለምትባለው ከተማ የምትቀርብ መንደር ውስጥ አማጺያን ትናንት ምሽት ባደረሱት ጥቃት በትንሹ 22 ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ወይም 'ኤዲኤፍ' የተባለው ቡድን ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።
የሀገሪቱ መከላከያ ኃይል በቅርቡ አማጺያኑ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈጸም መጀመራቸው ቡድኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን እንዲያደርስ አድርጎታል ተብሏል።
ጥቃቱ የደረሰባት መንደር ንቶምቢ የምትባል ሲሆን የአማጺ ቡድኑ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎ ሽጉጦችንና ቆንጨራ ይዘው እንደነበር ተገልጿል። የአካባቢው ባለስልጣናት ምናልባት ከታጣቂዎቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ የተገደሉ ዜጎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በአጎራባች አካባቢዎች ፍለጋ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የሟቾች ቁጥር ቀድሞ ከተነገረው ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በኡጋንዳ የተመሰረተው አማጺ ቡድኑ እስካሁን ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ የሌለው ሲሆን በዴሞክራቲክ ኮንጎ በምትገኘው ሰሜናዊ ኪቩ ግዛት በመንቀሳቀስ መንደሮችን ያሸብራል።
የዴሞክራቲክ ኮንጎ መከላከያ ኃይል ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ከመጀረ አንስቶ እስካሁን ከ 100 በላይ የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸው አልፏል።
በቅርበት በምትገኘው ደቡባዊ ኪቩ ግዛት ደግሞ የሀገሪቱ መከላከያ ኃይል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ አጉሮ እያሰቃያቸው እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ሰዎቹ ያሉበት ሁኔታ እጅግ ዘግናኝና አንዳንዶቹም እየሞቱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የቡድኑ አባላት በነዚህ ካምፖች ውስጥ ሳይኖሩ እንደማይቀር ተገምቷል።