ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ቤቶች ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን 27 ሰዎች ቀጠፈ
ትናንት ሁለት የአውሮፕላኑ ሰራተኞችን ጨምሮ 17 ሰዎች አሳፍሮ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዋ ጎማ ወደ ቤኒን ለማቅናት በተነሳ በአንድ በደቂቃ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች ላይ በተከሰከሰው አውሮፕላን ምክንያት 27 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።
ከ27ቱ ሟቾች ዘጠኙ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውም ሊታወቅ ችሏል።
ቢዚ ቢ የተባለ የግል አየር መንገድ ንብረት የሆነው ይህ አውሮፕላን ጎማ ውስጥ ማፔንዶ በተሰኘ መንደር ነው የተከሰከሰው።
የአውሮፕላኑ የመከስከስ መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን በማጣራት ላይ እንደሆኑ ባለስልጣናቱ ገልፀዋል።
አውሮፕላኑ ሶስት ጊዜ አየር ላይ እንደ እንዝርት ሾሮ ከዚያም እሳት ሲተፋ ማየቱን ዲጅሞ ሚዳር የተባለ የአይን እማኝ ለሮይተርስ ተናግሯል።
"አውሮፕላኑ ሲከሰከስ ወደ ወደቀበት ቦታ ሮጥን፣ ፓይለቱ ዲዲየር የሚባል ነው እናውቀዋለን። 'እርዱኝ እርዱኝ' እያለ ቢጮኸም እሳቱ በጣም ሃይለኛ ስለነበር ልናወጣው አልቻልንም" ብሏል።
የአቪዬሽን ደህንነት ቁጥጥር የላላ ነው በሚባልባት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአውሮፕላን አደጋ ይደጋገማል። አውሮፕላን ጥገና ችግርም ለተደጋጋሚ አደጋዎች በምክንያትነት ይቀመጣል።
የአገሪቱ ሁሉም የግል አየር መንገዶች በአውሮፓ እንዳይንቀሳቀሱ በአውሮፓ ህብረት ዕግድ ተጥሎባቸዋል።