ኬንያውያን መምህራን ሃብታችሁን አሳውቁ ተባሉ

ታትሟል

ኬንያውያን መምህራን ያላቸውን ሃብት ንብረት እንዲያሳውቁ ሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አስር ሺ ዶላር ወይም 300 ሺ ብር የሚጠጋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

በዚህ ሃብት ማሳወቅ መምህራን ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ በህዝብ ተቋማት ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ የመንግሥት ሰራተኞች እስከ ቀጣዩ ሁለት ሳምንት ድረስ ሃብት ንብረታቸውን በዝርዝር በማስቀመጥ ፎርም መሙላት ይጠበቅባቸዋል።

ሃብትና ንብረትን በመመዝገብ ሰራተኞች ጉቦ መቀበል አለመቀበላቸውን መቆጣጠር ያስችላል ተብሏል።

የኬንያ ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን እንደገለፀው ባለፈው ወር ወደ 843ሺ የሚጠጉ የመንግሥት ሰራተኞች ያላቸውን ሃብት፣ ንብረት፣ ባንክ ውስጥ ያላቸውን የገንዘብ መጠን፣ መሬት፣ ቤትና መኪኖቻቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሙስናን ለመቆጣጠር በመንግሥት መስሪያ ቤት ያሉ ግለሰቦች ኦዲት የሚደረጉበት ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።