ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግጭት በምትናጠው ቦሊቪያ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄ ቀረበ
የቦሊቪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጀኒኔ አኔዝ ምክር ቤቱ አዲስ ምርጫ የማካሄድ እቅድን እንዲያጸድቅ ጠየቁ።
የኢቮ ሞራሌስን ከሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ ቦሊቪያ በግጭት እየተናጠች ሲሆን፤ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ ለምርጫ ቀን ባይቆርጡም ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ጥያቄ አቅርበዋል።
ካለፈው ወር ጀምሮ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 ደርሷል። በሞራሌስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል ያለው ግጭትም አልረገበም።
ሞራሌስ፤ የጸጥታ ኃይሎች ደጋፊዎቻቸው ላይ "የዘር ጭፍጨፋ" እያደረጉ እንደሆነ ተናግረው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እርዳታ ጠይቀዋል።
የሞራሌስ ደጋፊዎች መዲናዋ ላ ፓዝን ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ዘግተዋል።
የቦሊቪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጀኒኔ አኔዝ የቀድሞው ምርጫ ውጤት ተሰርዞ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ አገራዊ መግባባት ይፈጥራል ብለው ያምናሉ። የፍትህ ሚንስትር አላርቮ ኮምብራ፤ ምክር ቤቱ በፍጥነት ጥያቄውን እንደሚቀበል ተስፋ አድርገዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የጸጥታ ኃይሎች ከሞራሌስ ደጋፊዎች ጋር ተጋጭተው ስምንት ሰዎች መሞታቸውን አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ሞራሌስ "የዘር ጭፍጨፋ" እየተፈጸመ ነው ቢሉም፤ የቦሊቪያ የአገር ውስጥ ሚንስትር አርቱሮ ሙራሎ፤ ሞራሌስ ደጋፊዎቻቸው መንገድ እንዲዘጉ ማዘዛቸውን ተናግረዋል። መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት ምግብ ማጓጓዝ እንዳልተቻለ ገልጸውም፤ "በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የተቃጣ ወንጀል ነው" ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2006 ላይ መንበረ ሥልጣን የጨበጡት የቀድሞው አርሶ አደር ሞራሌስ፤ የቦሊቪያን ምጣኔ ኃብት በማበልጸግ ቢመሰገኑም፤ ከሕግ ውጪ የሥልጣን ዘመናቸውን በማራዘማቸው ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።
በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ሞራሌስ በጠባብ የድምጽ ልዩነት አሸንፈዋል ቢባልም፤ ታዛቢው 'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ አሜሪካን ስቴትስ' ምርጫው መጭበርበሩን ይፋ አድርጓል።
ሞራሌስ ሌላ ምርጫ ለማካሄድ ቢስማሙም በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ካርሊስ ሜሳ፤ ሞራሌስ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። ይህንን ተከትሎ በተነሳ አለመረጋጋር ሳቢያ ሞራሌስ ሥልጣን ለቀው ወደ ሜክሲኮ መሸሻቸው ይታወሳል።