የሂትለር ቤት ፖሊስ ጣቢያ ሊሆን ነው

ታትሟል

አዶልፍ ሂትለር የተወለደበት ኦስትሪያ ውስጥ የሚገኝ ህንፃ ወደ ፖሊስ ጣቢያነት እንደሚለወጥ ተገለጸ።

የኦስትሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ዎልፍጋንግ ፔሽሮን፤ ህንፃው ናዚዎችን ለመዘከር እንደማይውል በአጽንኦት ተናግረዋል።

ሂትለር ከተወለደ በኋላ ለጥቂት ሳምንታት በ17ኛው ክፍለ ዘመን በተሠራው ህንፃ ውስጥ በሚገኝ ቤት ኖሯል።

ህንፃው ምን ይደረግ የሚለው ለረዥም ጊዜ ሲያከራክር ቆይቷል።

የኦስትሪያ መንግሥት ግራ ዘመሞች ህንፃውን እንዳይጎበኙ ለማድረግ ለህንፃው የቀድሞ ባለቤት አከራይቶት ነበር። በአንድ ወቅት ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ማዕከል ነበር።

ህንፃው ለዊልቸር ተጠቃሚዎች ምቹ ሆኖ እንዲሠራ የቀረበውን ሀሳብ የህንፃው ባለቤት ጀርሊንድ ፖመር ስላልተቀበሉት፤ ማዕከሉ ተዘግቷል። የህንፃው ባለቤት ማንኛውም አይነት እድሳት ከልክለው፣ ህንፃውን ለመንግሥት አልሸጥም ብለውም ነበር።

ከአምስት ዓመት በፊት ህንፃውን የስደተኞች መጠለያ ለማድረግ ታቅዶ ሳይሳካ ቀርቷል። ከአራት ዓመት በፊት መንግሥት ህንፃውን በ810,000 ዩሮ ገዝቶታል።

ህንፃው ይፍረስ የሚሉ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ህንፃው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጥበት አልያም እርቀ ሰላም የሚወርድበት እንዲሆን የጠየቁም ነበሩ።

ሂትለር የተወለደው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1889 ብራውናው አም ኢን በተባለ ቦታ ነበር። ቤተሰቦቹ በህንፃው ውስጥ ለጥቂት ሳምንታት ኖረው ወደ ሌላ ቤት ተዘዋውረዋል። ሂትለር ሦስት ዓመት ሲሆነው ደግሞ ወደ ሌላ ከተማ ሄደዋል።

ሂትለር በናዚ ጀርመን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለመነሳቱ እንዲሁም ስድስት ሚሊየን አይሁዳውያን በግፍ ለመገደላቸው ምክንያት ነው።