ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለመቀበል ዘረኝነትን ይከተላል የሚለው ክስ ውድቅ ተደረገ

ታትሟል

ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ቅበላ ቢሮ እስያዊ አሜሪካዊያን አመልካቾችን ለመቀበል እንደማያገል ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ በነበረው የፍርድ ቤት ውሳኔ ተገለፀ።

የችሎቱ ዳኛ ለሐርቫርድ ከሚያመለክቱና ተመሳሳይ ውጤት ካላቸው ነጭ፣ጥቁርና፣ ሂስፓኒክ ተማሪዎች ከእስያዊ አቻዎቻቸው ይልቅ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ አሊሰን ዲቡሮህስ እንዳሉት ችሎቱ "በአግባቡ የተቀመጠን" የመግቢያ መስፈርት ሊያፈርስ አይችልም።

ይህ የፍርድ ቤት ውሎ ዩኒቨርስቲው ለሚከተለው በታሪክና በሌሎች ጉዳዮች የተገፉ አካላትን መቀበያ መስፈርት ላይ እንደሚካሄድ ሪፍረንደም ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

ጉዳዩ በይግባኝ የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊደርስ ይችላል ተብሏል።

ሐርቫርድ በአሜሪካ ዝነኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲሆን በየዓመቱ ከ42 ሺህ አመልካቾች ውስጥ አንድ ሺህ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል።

ይህ ክስ ሐርቫርድ ላይ የቀረበው ተማሪዎች ፍትሃዊ የቅበላ መስፈርት በማሊ ቡድን ሥር ከተሰባሰቡ በኋላ ነው።

ከዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ወግ አጥባቂው ኤድዋርድ ብለም፣ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ የተገለሉትን ለመደገፍ ታስቦ የተቀመጠውን የዩኒቨርስቲውን የተማሪዎች መቀበያ መስፈርት ይቃወማል።

እርሱ እንደሚለው ይህ የምሁራን ማፍሪያ የሆነ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ዘረኝነት ላይ ተጠምዷል። ለዚህም ምክንያቴ ያለው ኢሲያዊ አሜሪካውያን ወደ ተቋሙ ለመግባት ከፍተኛ ነጥብ እንዲያመጡ መጠበቁን ነው።

ሐርቫርድ ኮታን በመጠቀም የዘር ልዩነቱን ለማስተካከል እየሰራ ነው በማለት፤ ይህ ደግሞ በፌደራል ሕጉ ላይ የተከለከለ ነው ሲል ያብራራል። በተቋሙ ውስጥ ያሉትን እስያዊ ተማሪዎች ቁጥር መገደብ የዘረኝነት መልክ ነው ሲል ነው ያስቀመጠው ኤድዋርድ።

ወደ ተቋሙ ለመግባት ዘር መሰረት ባይሆን ኖሩ በቁጥር ላቅ ያሉ እስያውያን ይገቡ ነበር የሚለው ኤድዋርድ፣ ምክንያቱም ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ በርካታ እስያውያን አሉ ሲል ይገልፃል።

ሐርቫርድ ግን ተማሪን ለመቀበል ሁሉን አቀፍ መስፈርት እንደሚጠቀም ገልጾ ዘር ትንሹ መስፈርታችን ነው ሲል አስተባብሏል።

በዩኒቨርስቲው በአሁኑ ሰዓት የእስያ ዝርያ ያላቸው ተማሪዎች ቁጥር እያደገ ሲሆን ከአጠቃላይ ተማሪዎቹ 23 በመቶ ያህሉን ይይዛሉ።