ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስም መመሳሰል ምክንያት ባልፈጸመው ግድያ ተከሶ ፍርድ ቤት የቀረበው ግለሰብና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች
ኢትዮጵያ
• በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እስር ላይ ያሉት የቀድሞው የሜቴክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው አቶ ኢሳይያስ ዳኘው፣ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ የደህንነት አቶ ተስፋየ ኡርጌ በዛሬው ዕለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቡ።
ፍርድ ቤቱ የሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው አቶ ኢሳይያስ ዳኘው ጉዳይን ለመመልከት ጊዜ ባለመኖሩ ለረቡዕ ህዳር 26 ቀጠሮ ይዟል።
ኬንያ
• በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን ዛሬ ጠዋት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ በእግራቸው ወደ ስራ ሲሄዱ እንደነበር ተዘገበ።
በእግራቸው ለመሄድ የተገደዱት ደግሞ የከተማዋ ባለስልጣናት ታክሲዎች በዋና ዋና መንገዶች እንዳይሄዱ በመከልከላቸው ነው።
ናይጄሪያ
• የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪ በህይወት የሉም፤ እሳቸውን የሚመስል ሰው ነው ሃገሪቱን እየመራት ያለው የሚለው ዜና ውሸት እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ተናገሩ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨው ዜና መሰረት ፕሬዝዳንቱን የሚመስል ጀብሪል የተባለ ሱዳናዊ ነው ፕሬዝዳንት የሆነው።
እንግሊዝ
• የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ቶተንሃም ደጋፊ የሆነ ግለሰብ የአርሰናል ተጫዋች ላይ ሙዝ በመወርመሩ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የአርሰናሉ ጋቦናዊ አጥቂ ኦባሚያንግ ግብ ሲያስቆጥር ሙዙን የወረወረው ግለሰብ የወደፊት ጨዋታዎችም እንዳይመለከት ታግዷል።
ፊንላንድ
• ፊንላንድ ያለ ካፒቴንና ሌሎች ሰራተኞች ለብቻው ባህር ማቋረጥ የሚችል መርከብ ሰራች።
መርከቡን መሬት ላይ ሆነው የሚቆጣጠሩ የባህር ሃይል አባላት ያሉ ሲሆን፤ በቅርቡ ረጅም ርቀት መጓዝ ይጀምራል ተብሏል።
ህንድ
• ህንድ ውስጥ አንዲት ሴት ጾታዊ ጥቃት በፈጸሙባት ሁለት ወንዶች በእሳት ተቃጥላ በሞት አፋፍ ላይ እንደሆነች ተገለጸ።
ጥቃቱ የደረሰባት ሴት ጉዳዩን ለፖሊስ ልትናገር እየሄደች ሳለ በእሳት ያቃጠሏት ሁለቱም ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኳታር
• ኳታር ኦፔክ ከተባለው የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር እራሷን አገለለች።
ውሳኔው የተሰማው አምራች ሃገራቱ ከሚያደርጉት ዓመታዊ ስብሰባ ቀናት በፊት ነው።
የመን
• የተባበሩት መንግስታት በየመን ሰላም ለማውረድ በማሰብ ጉዳት ለደረሰባቸው የሁቲ አማጺያን እርዳታ ሊያደርግ ነው።
50 ወታደሮች በአውሮፕላን ተጓጉዘው ህክምና የሚደረግላቸው ሲሆን፤ እርምጃው ሰላማዊ ድርድር ለማድረግ ወሳኝ ነው ተብሏል።
አውስትራሊያ
• አውስትራሊያ ውስጥ አንድ ግለሰብ በስም መመሳሰል ምክንያት ባልፈጸመው የነብስ ማጥፋት ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ከጥቂት ውዥንብር በኋላ ግን ትክክለኛው ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ30 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ቻይና
• ቻይና እጅግ የተጋነኑ ወጪዎች አንዳንዴም ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት የሚፈጸሙባቸው የሰርግ ስነስርአቶችን ልትቆጣጠር ነው።
ሰርጎቹ አላስፈላጊ ወጪ የሚበዛባቸውና ከማህበረሰቡ ባህል ያፈነገጡ ናቸው ብለዋል የቻይና ባለስልጣናት ።