ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብሩንዲው የቀድሞ መሪ ቡዮያ ላይ የእሥር ትዕዛዝ መውጣቱ የአፍሪቃ ሕብረትን አስቆጣ
የአፍሪቃ ሕብረት ብሩንዲ ሰላምን አደጋ ላይ እያጣለች ነውና አደብ ልትይዝ ይገባል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የቀድሞ የሃገሪቱ መሪ ፒየር ቡዮያ እና ሌሎች 16 ባለሥልጣናት ምርጫ አሸነፈው ወደሥልጣን የመጡት ዳዳየን በማስገደል ወንጀል ተጠርጥረው ዓለም አቀፍ የእሥር ትዕዛዝ የቡሩንዲ መንግሥት አውጥቶባቸዋል።
በፈረንጆቹ 1993 ነበር ዘራቸው ከሁቱ የሚመዘው ፕሬዚዳንት ሜልቾይር ዳዳየ በሀጋሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫ በማሸነፍ ሥልጣን የያዙት። ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ተገደሉ። የፕሬዚዳንቱ ግድያም ሃገሪቱን የከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ማገዳት።
ለ12 ዓመታት ያህል በዘለቀውና አናሳ ቁጥር ባላቸው ቱትሲዎች የሚመራው የወታደር ክፍልና ሁቱዎች ባደረጉት የእርስ በእርስ ጦርነት ቢያንስ 300 ሺህ ያህል ሰዎች ተገድለዋል።
የቀድሞው መሪ ቡዮያ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ በወታደሮቻቸው ታግዘው ሁለት ጊዜ ሥልጣን ጨብጠዋል።
በርካቶች ቡዮያ በአህጉረ አፍሪቃ ትልቅ የዲፕሎማሲ ሰው አድርገው ይወስዷቸዋል።
ባዮያ የእሥር ትዕዛዙን በተመለከተ ''አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ቀውስ ለማስረሳት ሆነ ተብሎ እኔ ላይ የእሥር ትዕዛዝ ወጣ'' በማለት ግለጫ አውጥተዋል።
የሃገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ እንዳገዙ የሚነግርላቸው ቡዮያ ሃገሪቱ ከቀውስ ወጥታ ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደታቀና እንዳገዙ ይነገርላቸዋል።
ብሩንዲ አሁን ያለችበት ቀውስ ውስጥ የገባችው አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ፒየር ንኩሪንዚዛ ሕገ-መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ጊዜ ለምርጫ እወዳደራለሁ በማለታቸው ነው።
የዳዳየ ግድያ የኔን ክብር ለመንካት ተደርጎ ነው የቀረበው የሚሉት የ69 ዓመቱ ቡዮያ በአሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በማሊ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ይህኑ የእሥር ትዕዛዝ ተከትሎም የአፍሪቃ ሕብረትም ብሩንዲ ሰላም እንዲደፈርስ እያደረገች ነው ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አውጥቷል።
በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ይዘው የነበረው ዳዳየ ከአራት ወራት በኋላ ቢገደሉም የግድያቸው ምስጢር አሁንም አከራካሪ እንደሆነ አለ።
ንኩሩንዚዛ በ2020 ለሚደረገው ምርጫ ራሳቸውን እየዘጋጁ ሲሆን፤ ከምስራቅ አፍሪቃ መንግሥታትም ይሁን ከአፍሪቃ ሕብረት ግን ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል።