የእንግሊዝ ክለቦች ለተጫዋች ግዥ 1.6 ቢሊዮን ዶላር አወጡ

የእንግሊዝ ፕሪሜርሊግ ተዘጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእንግሊዝ ፕሪሜርሊግ ተዘጋ
ታትሟል

ትናንት ብሪታኒያ ውስጥ ሁለት ክስተቶች በተመሳሳይ ሰዓት እልባት አግኝተው በብዙዎች ዘንድ ግርምትን አጭሯል። ሁለቱም የተጠናቀቁት በየራሳቸው መንገድ ቢሆንም ትናንት እኩለ ሌሊት ስፖርትና ፖለቲካ ተመሳሳይ ሰዓት ላይ ተገጣጥመዋል፤ በእንግሊዝ ሰዓት አቆጣጠር 23፡00 ላይ።

ለሦስት ዓመታት ሲንከባለል የነበረው የብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት የመውጣት ሂደት ፍጻሜውን አግኝቶ በመላዋ ብሪታኒያ ሲበሰር፤ በዚያችው ቅጽበትም የእንግሊዝ ፕሪሜየር ሊግ የጥር የዝውውር መስኮት ተዘግቷል።

የዝውውር ወሩ ስም ያላቸው ተጫዋቾችን ብዙም ሳይዳፈር በአብዛኛው አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ፕሪሜር ሊጉ በማምጣት ተጠናቋል።

በማጠናቀቂያ ሰዓቱ ላይ የፈረሙት ጃሮድ ቦውን እና ኦዲዮ ኢጋሎ በመጨረሻዋ ቀን በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ የተገዙ ተጫዋቾች ናቸው።

በመጨረሻዋ ቀን ዌስትሃም ዩናይትድ የሃል ሲቲውን አጥቂ ጃሮድ ቦውን በ18 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈርሟል። በውድድር ዘመኑ በጥር የዝውውር የመዝጊያ ዕለት ብቻ የወጣ ከፍተኛ ገንዘብ ሆኖም ተመዝግቧል።

ይሁን እንጂ በጥር የዝውውር ወር የመጨረሻ ቀን እስከዛሬ ከወጣው ከፍተኛ ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ከ2010 እ.አ.አ ወዲህ ትንሹ ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቧል።

በወሩ አጠቃላይ የእንግሊዝ ክለቦች 230 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ አድርገው ተጫዋቾችን የገዙ ሲሆን በታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ከዚህ ገንዘብ መካከል ታዲያ በመጨረሻዋ ቀን 25 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነው ወጪ የተደረገው።

እንደአጠቃላይ ደግሞ በዚህ የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ክለቦች ተጫዋች ለመግዛት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ፓውንድ አውጥተዋል። ይህም 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ፓውንድ ከወጣበት የ2017/18 የውድድር ዘመን ቀጥሎ በታሪክ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ሁለተኛው የውድድር ዘመን ያደርገዋል።

ከዚህ የውድድር ዘመን ውጪ በጥር የዝውውር ወር በዝውውሩ የመዝጊያዋ ዕለት ከ30 ሚሊዮን ፓውንድ በታች ወጪ የተደረገበት የውድድር ዘመን 2010 እ.አ.አ ነው። 10 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነበር ወጪ የተደረገበት።

ከፍተኛው ደግሞ 2018 እ.አ.አ ሲሆን በመዝጊያው ዕለት ብቻ 180 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ተደርጎበታል።

በዚህ የዝውውር ወር ቼልሲ ምንም ተጫዋች ባለማስፈረም ብቸኛው ክለብ ነው። ማንችስተር ዩናይትድ የስፖርቲንግ ሊዝበኑን ብሩኖ ፈርናንዴዝን በ47 ሚሊዮን መነሻ ዋጋ ያሰፈረመ ሲሆን በሂደት ግን የተጫዋቹ ዋጋ እስከ 67.7 ሚሊዮን ፓውንድ ያድጋል ተብሏል።

ሸፊልድ ዩናይትዶች ሳንዴር በርግን በ22 ሚሊዮን ፓውንድ በማስፈራም የራሳቸውን ክብረወሰን አሻሽለዋል።

በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች የዝውውር ጊዜያቸውን አጠናቅቀዋል። ስፔን፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይና ሆላንድ እንደ እንግሊዝ ሁሉ የዝውውር ጊዜያቸውን በፈረንጆቹ ጥር 31 ትናንት ሌሊት የብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት ጋር እኩል የዘጉ ናቸው።

የፖርቱጋል ክለቦች ደግሞ በገበያው እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ሁለት (በኢትዮጰያ እስከ ጥር 24) ድረስ ይቆያሉ። በተጨማሪም የሩሲያ፣ የቻይናና የአሜሪካ ክለቦች አሁንም አዲስ ተጫዋቾችን መቀበል ከሚችሉት መካከል ናቸው።