ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሴኔጋል ሆስፒታል ውስጥ በተቀሰቀሰ እሳት አስራ አንድ ጨቅላዎች ሞቱ
በሴኔጋል ምዕራባዊ ክፍል ቲቫኖዋኔ በተባለች ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ላይ በተነሳ እሳት 11 ገና የተወለዱ ህጻናት ህይወት ማለፉን የአገሪቱ ፕሪዝዳንት ተናግረዋል።
ማሜ አብዱ አዚዝ በተባለው ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ላይ እሳት መቀስቀሱን ፕሬዝዳንቱ ማኪ ሳል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የእሳቱ መነሻ በኤሌክትሪክ መስመር ላይ በተፈጠረ ችግር ሳይሆን እንደማይቀር ቅድመ ሪፖርት አመላክቷል።
ከአደጋው 3 ህጻናትን መታደግ መቻሉን የከተማው ከንቲባ ዴሞባ ዲፖ ሳይ ገልጸዋል።
ከንቲባው እሳቱ በፍጥነት መዛመቱን የተናገሩ ሲሆን የአደጋ ተካላካይ ሰራተኞች በስፍራው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንን ዋቢ አድርጎ ኤ ኤፍ ፒ እንደዘገበው ሆስፒታሉ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መሰጠት የጀመረ ነው።
"ለእናቶቹ እና ለቤተሰቦቻቸው የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳል በትዊተር መልዕክታቸው።
በዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ጄኔቫ የሚገኙት የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር አብዶላይ ዲዮፍ በበኩላቸው "ክስተቱ ያለመታደል ነው። ህመሙም እጅግ መራር ነው" ብለዋል።
ጉባኤውን አቋርጠው ወደ ሀገር እንደሚመለሱ የሚጠበቀው ሚኒስትሩ አደጋው ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ክስተቱ በሴኔጋል ያለውን የጤና ስርዓት ላይ ቅሬታ በመፍጠር በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
የተቃዋሚ ፓርቲ እና የፓርላማ አባል የሆኑት ማማዱ ላማይኔ ዲያሎ በትዊተር ገጻቸው መንግሥትን የኮነኑ ሲሆን "በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ከዚህም በላይ ህጻናት ተቃጥለዋል ይህም ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ክስተት ያጋጠመ ሲሆን በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል በተነሳ እሳት አራት ጨቅላ ህጻናት ህይወታቸው አልፏል።
11 ጨቅላ ህጻናትን የቀጠፈው ክስተት ከመሰማቱ በፊት በአገሪቱ ለ 20 ሰዓት ያማጠች አንዲት እናት ህክምና ለማግኘት ተማጽኖ አቅርባ ሳይሳካ በመቅረቱ እሷና ያልተወለደ ልጇ መሟታቸው ከተነገረ በኋላ ነው። ይህም በሀገሪቱ ቁጣን ቀስቅሷል።