በናይጄሪያ የክርስቲያን ተማሪ መገደል ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ የሰዓት እላፊ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባሳለፍነው ሳምንት የአንድ ክርስቲያን ተማሪ መገደልን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ ተቃዋሚዎች መንገድ ላይ በመውጣት መቃወማቸውን ተከትሎ በናይጄሪያዋ ሶኮታ ከተማ ለ24 ሰአት የሚቆይ የሰአት እላፊ ታውጇል።
ዲቦራህ ሳሙኤል የተባለችው ተማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ከሀይማኖታዊ ስርአት ውጪ በሆነ መልኩ እንዲሁም እስልምና እምነትን የሚያንቋሽሽ መልዕክት ዋትስአፕ በተሰኘው በማህበራዊ ሚዲያ በኩል አጋርታለች በሚል ሙስሊም ተማሪዎች በቡድን ከደበደቧት በኋላ አቃጥለዋታል።
የተማሪዋ ግድያ በመላው ናይጄሪያ በሚገኙ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ከፍተኛ ተቃውሞን አስከትሏል። በርካቶችም በሐይማኖት ስም የሚደረጉ ግድያዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውና ሊወገዙ እንደሚገባ እየገለጹ ነው።
ትናንት ቅዳሜ ዕለት ተቃዋሚዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ጎማ ያቃጠሉ ሲሆን ፖሊስ ደግሞ በምላሹ አስለቃሽ ጭስ ለመተኮስ ተገድዷል።
አንዳንድ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የሶኮቶ ሱልጣን እና ናይጄሪያ ውስጥ ከፍተኛ የእስልምና አባት ተደርገው የሚቆጠሩት ሙሀመድ ሳድ አቡባካር መኖሪያ ቤትን በመክበብ ጥያቄያቸውን አሰምተዋል።
ሱልጣኑ ከተማሪዋ ግድያ በኋላ ተግባሩን በእጅጉ የተቹት ሲሆን ይህንን ወንጀል የፈጸሙትን ተይዘው ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብለው ነበር።
የሶኮቶ አስተዳዳሪው አሚኑ ዋዚሪ የሰአት እላፊውን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ''ስለ ሰላም ሲባል እባካችሁ በሰላም ወደ ቤታችሁ ተመለሱ'' ብለዋል።
ናይጄሪያ በአፍሪካ ትልቁን የሕዝብ ቁጥር የያዘች አገር ስትሆን ሰሜናዊው ክፍል በብዛት የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚበዙ ሲሆን በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ አብዛኛው ዜጋ አክራሪ የክርስትና እምነት ተከታይ ነው።
ናይጄሪያ ውስጥ ሐይማኖታዊ ውጥረትና ግድያዎች አዲስ አይደሉም። በተለይ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎች አካባቢ የሚገኙ ግዛቶች ጠበቅ ያሉ የሸሪአ ሕጎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
ይህ ደግሞ ሐይማኖቱን የሚያንቋሽሹና ተገቢ ያልሆነ ተብሎ የሚቆጠር ነገር የሚፈጽሙት ላይ እስከ ግድያ የሚደርሱ ቅጣቶችን ይፈቅዳል።
ፕሬዝደንት ሙሀመዱ ቡሃሪ በዲቦራህ ሳሙኤል ግድያ በእጅጉ ማዘናቸውና በምንም አይነት ሁኔታ እንደማይቀበሉት በመግለጽ ገለልተኛ የሆነ ምርመራ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በናይጄሪያ ትልቁ የክርስቲያኖች ጥምረት በበኩሉ መንግስት በአፋጣኝ ወንጀለኞቹን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።












