ኮቪድ -19፡ ሰሜን ኮሪያ የኮቪድ ወረርሽኝ በመከሰቱ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል አዘዘች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሰሜን ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ጥብቅ ብሔራዊ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል አዘዘች።
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በዋና ከተማዋ ፕዮንግያንግ የኦሚክሮን ወረርሽኝ መከሰቱን የዘገበ ሲሆን ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ግን አልገለጸም።
ኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ ( ኬሲኤንኤ) የወረርሽኙን መከሰት የአገሪቷን የለይቶ ማቆያ ሕግ የጣሰ "ትልቅ አደጋ " ነው ያለ ሲሆን፣ የአገሪቷ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለብሔራዊው አደጋ ምላሽ ለመስጠት አስቸኳይ ስብሰባ እያደረጉ ነው ብሏል።
ይሁን እንጂ ታዛቢዎች ቫይረሱ አሁን የተከሰተ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ በአገሪቷ እንደነበር ያምናሉ።
ሰሜን ኮሪያ በቻይና የተሰራውን ሲኖቫክስስ እንዲሁም አስትራዜኒካ ክትባትን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ የኮቪድ 19 ክትባት ለሕዝቦቿ አልሰጠችም።
አገሪቷ ቫይረሱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሥርጭቱን ለመከላከል ያለመችው ድንበሮቿን በመዝጋት ነው። ይህም ወደ አገሪቷ የሚገቡ መሠረታዊ ፍጆታዎች እንዲቀንሱ በማድረጉ አገሪቷን ለከፋ ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ እና የምግብ እጥረት አጋልጧታል።
እንዲህም ሆኖ ወረርሽኙ ሊከሰት እንደሚችል ምልክቶች ነበሩ።
ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ ያልተረጋገጡና በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝገብዋል። ጎረቤት አገሯ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያም ወረርሽኙ ተከስቶባቸዋል። ቻይና አሁን ላይ የኦሚክሮንን ወጀብ ለመቆጣጠር እየታገለች ነው።
ባለፈው ሰኔ ወር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ፕሬዚደንት ኪም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ስለተከሰተው አሳሳቢው ክስተት ባለሥልጣናትን መተቸታቸውን የዘገቡ ሲሆን ስለጉዳዩ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
መስከረም ወር መንግሥት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም የበሽታ መከላከያ ልብስ በመልበስ ወታደራዊ ሰልፍ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ አንዳንድ ተንታኖች ልዩ ኃይሉ የተፈጠረው የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከል አንዲሳተፉ እንደሆነ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።














