ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ወደ ሥራ ቦታ መመለስና ፈተናዎቹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሁለት ዓመት በኋላ በርካታ የዓለማችን ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው በየቤታቸው ከመስራት ወደ ቢሮ ስለመመለስ እንዲያስቡ እያደረጉ ነው። አብዛኞቹም ወደ ሥራ ቦታቸው መመለስ ጀምረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥር ወር ላይ "ሁሉም አሜሪካውያን ወደ ሥራ ገበታቸው በመመለስ የተዳከሙትን ከተሞች እንደገና ማነቃቃት መጀመር አለባቸው" ብለው ነበር።
ባይደን ዜጎች ወደ ሥራ ቦታቸው መመለስ እንዲጀምሩ ጥሪ ያቀረቡት ብቸኛው መሪ አይደሉም። "ተፈጥሮ ከቤት ሆና አይደለም የምትሰራው" ያሉት ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ናቸው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ይዟቸው ከመጡ ጉዳዮች መካከል ከቤት መስራት አንዱ ነው። ሆኖም ከቤት መስራት ማንን ይጠቀማል? ማንን ይጎዳል? በሚል ሲያከራክር ቆይቷል። ከቤት በመስራት አሰሪም፣ ሠራተኛም እየተጠቀሙ ነው። ሠራተኞች ገንዘብ እና ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ ሲያግዝ፣ አሰሪዎችን ደግሞ ለቢሮ ቦታ እና ሥራ ማስኬጂያ የሚያወጡትን ወጪ ቀንሷል።
ሆኖም ሠራተኞች ከቤት ሲሰሩ የሚሰሩበት መጠን ወይም ምርታማነታቸው ዝቅ ይላል በሚል የሚከራከሩም አሉ። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሰዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ለመሄድ የሚያጠፉትን ጊዜ በመቆጠብ በምሽት እና በእረፍት ሰዓታቸው ብዙም ሳይረበሹ እንዲሰሩ ያስችላል የሚሉም አሉ።
መሪዎች ዜጎቻቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መፈለጋቸው የሚያስገርም አይደለም። በየቀኑ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከሌሉና ሁሉም አይነት ንግድ ከተስተጓጎለ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዜጎች በየቀኑ ለትራንስፖርት የሚያወጡት በአጠቃላይ 82 ሚሊየን ፓውንድ ሲሆን፣ አሜሪካ ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ለትራንስፖርት በየዓመቱ ቢያንስ ከ2 ሺ እስከ 5 ሺ ዶላር ያወጣ ነበር።
ነገር ግን እዚህ ጋር ትልቅ ችግር አለ። ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰዎች ስለትራንስፖርት ወጪ እምብዛም ሳይጨነቁ፣ ውጪ ምግብ ስለመመገብ ሳያስቡ እንዲሁም በሥራ ገበታቸው ላይ ሲሆኑ ስለሚለብሱት ልብስ ሳይጨነቁ ነው የከረሙት።
በአንድ ጊዜ ወደ ሥራ ገበታችሁ ተመለሱ ሲባሉ ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች አንጻር ወጪው ከፍ እንደሚልባቸው ያስባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሁሉም ነገር ዋጋ ባለፉት ሁለት ዓመታት በእጅጉ ጨምሯል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲሁም የገንዘብ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ሰዎች ወደ ቢሮ ሄደው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ምን ያህል እንደሚያስወጣቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ቢሮ ስለመመለስ እምብዛም ደስተኞች አይደሉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዮናስ አስፋው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ነው የሚሰራው። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቤቱ ሆኖ ነበር ሥራውን የሚያከናውነው። ነገር ግን ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ቢሮ እንደተመለሰና ነገሮች ሁሉ እንደከበዱት ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ከቤት በምሰራበት ጊዜ ብዙም ወደ ውጪ አልወጣም ነበር። ምግቤን የማበስለው እራሴ ነኝ። የትራንስፖርትም ሆነ የምግብ እንዲሁም የቡና ወጪ አልነበረብኝም። አሁን ወደ ቢሮ ተመልሻለሁ። የግል መኪና ስለሌለኝ የምንቀሳቀሰው በታክሲ ሲሆን ወጪው በራሱ በጣም ከባድ ሆኗል። ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ለቡና ወጣ ማለት እንዲሁም ምሳ መብላት ሚሉት ጉዳዮች በየቀኑ ስለሚደረጉ በጣም ከፍተኛ ወጪ አለው" ሲል ያስረዳል።
ዮናስ እንደሚለው ወደ ሥራ በመመለሱ ደስተኛ አይደለም። ምቾቱን ጠብቆ ሲፈልግ ሶፋ ላይ አንዳንዴም አልጋው ላይ ሆኖ ነበር ሥራውን የሚያከናውነው። "ወደ ቢሮ ስለመመለስ ሳስብ ትንሽ ጭንቀት ተሰምቶኝ ነበር። አብዛኛዎቹም ባልደረቦቼ መልመድ እንዳስቸገራቸው ነግረውኛል" ይላል።
ለንደን ውስጥ የሚገኝ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት የምትሰራው ክሌር ወደ ቢሮ መመለስ ቀላል የማይባል ወጪ እንዳለው ታስረዳለች።
"ወደ ሥራ በተመለስኩበት የመጀመሪያ ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት። ወጪው የሚቀመስ አይደለም። ከወረርሽኙ በፊት ለትራስፖርት፣ ለምግብ፣ ለውሀ እና ቡና ወይም ሻይ አወጣው የነበረውን ወጪ አስቀምጠቀው ነበር። በስድስተኛ ወር መጨረሻ ላይ ይህ ገንዘብ 6 ሺ ፓውንድ ደርሶ ነበር። ልክ ወደ ቢሮ መመለስ ስንጀምር ወጪው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተረድቻለው" ትላለች።
ነገሮችን ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ቀላል የሚባለው የትራንስፖርት ዋጋ እንኳን በእጅጉ መጨመሩ ነው። ለምሳሌ ከወረርሽኙ በፊት 35 ፓውንድ ያወጣ የነበረ የባቡር ቲኬት ዋጋ አሁን ላይ 50 ፓውንድ ደርሷል። ምንም እንኳን የክሌር ቀጣሪ ድርጅት ከወረርሽኙ መልስ ወደ ሥራ ለሚገቡ ሠራተኞቹ የደሞዝ ጭማሪ ቢያደርግም በቂ እንዳልሆነ ትናገራለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለሁለት ዓመታት ሳያገኟቸው ከቆዩ ባልደረቦቻቸው ጋር መገናኘት በራሱ ትንሽ ግራ የመጋባት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ከባድ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ድርጅቶቹ በሁለት ዓመታት ውስጥ አዳዲስ ሠራተኞችን ቀጥረው ከሆነ በአንድ ጊዜ ከአዲስ ሰዎች ጋር በአካል መገናኘትና ስለ ሥራ ማውራት አስጨናቂ ሊሆን ይችላል።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኡሙስ በበኩላቸው ከኮቪድ-19 በኋላ ከሰዎች ጋር መነጋገር እንደከበዳቸውና የሁሉም አገልግሎት ዋጋ መጨመር በጣም እንዳስደነገጣቸው ይናገራሉ።
"ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሮ ስመለስ በጣም ነበር የደነገጥኩት። በስልክ አልያም በቪዲዮ ጥሪዎች ብቻ ሳገኛቸው የነበሩ ባልደረቦቼን በአካል ሳገኛቸው ትንሽ ግራ ተጋብቼ ነበር። እንዴት ማውራት እንዳለብኝም አስቤ ነበር። በሌላ በኩል ሁሉም ነገር ደግሞ በጣም ውድ ሆኗል። የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሯል ስል የሰሙኝ ሰዎች ለምን በሳይክል አትመላለስም ይሉኛል። እንዴት ነው በቀን ሁለት ጊዜ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በሳይክል መጓዝ የምችለው?" ሲል የሁኔታውን ከባድነት ይናገራል።
ሰዎች ከቤታቸው ሆነው በሚሰሩበት ወቅት የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የቡና እንዲሁም የልብስ ወጪያቸው በእጅጉ እንደቀነሰና ቢሮ ስለመመለስ ሲያስቡ የሚያስፈራቸው እሱ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁንም ድረስ ከቤታቸው የሚሰሩ ሰዎች በምን አይነት ሁኔታ ተመልሰው ወደ ቢሮ መግባት እንደማይፈልጉ ነው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩት።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ ምንም እንኳን መንግሥትም ሆነ ድርጅቶች የደሞዝ ማሻሻያዎችን ቢያደርጉም ከኑሮ ውድነቱ አንጻር የገንዘባቸው የመግዛት አቅም እስከ ሁለት በመቶ መቀነሱን ያሳያል።
በሌላ በኩል አሜሪካ ውስጥ የሠራተኞች ደሞዝ 4 በመቶ የጨመረ ቢሆንም የአብዛኞቹ ነገሮች ዋጋ ደግሞ በ7 በመቶ ጨምሯል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2020 ምንም አይነት ጭማሪ ለሠራተኞች ያልተደረገ ሲሆን የኑሮ ውድነቱ ደግሞ ከ4 በመቶ በላይ ጨምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ውስጥ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ዜጋ በግል መኪና የሚንቀሳስ ሲሆን በቅርብ ወራት የተስተዋለውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በርካቶች መኪናቸውን በማስቀመጥ በሕዝብ ትራንስፖርት ለመጠቀም እየተገደዱ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት አሜሪካ ውስጥ አንድ ጋሎን ነዳጅ 2.87 ዶላር ነበር የሚሸጠው። ነገር ግን አሁን ላይ ዋጋው ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ በማሳየት 4.10 ዶላር ደርሷል።
ደቡብ አፍሪካም በተመሳሳይ ቀላል የማይባሉ የዋጋ ጭማሪዎችን አስተናግዳለች። "የ2020 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ የሠራተኞች ደሞዝ እምብዛም ጭማሪ ሳያሳይ የነዳጅና ሌሎች መሰረታዊ ቁሳቁሶች ዋጋ በእጅጉ ጨምሯል" ትላለች ጆሀንስበርግ ውስጥ የቢሮ ኃላፊ የሆነችው ትሬሲ ቤንሰን። ደቡብ አፍሪካ አሁን ላይ አብዛኞቹን የኮቪድ ገደቦች አላልታለች።
"አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ቢሮ እንድመለስ ነው የተነገረኝ። ነገር ግን ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ነው። በተለይ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ብቻውን ወጪዬን ያቃውሰዋል። በጣም ከባድ ነው" ትላለች ትሬሲ።
በመላው ዓለም ሁሉም ነገር ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ተከትሎ ሠራተኞች ከቤት ሆነው መስራታቸውን መቀጠል ቢያስቡ አይፈረድባቸውም። ይህንን የተረዱ የሚመስሉ አንዳንድ ድርጅቶችም ለሠራተኞቻቸው የተለያዩ አማራጮችን እያቀረቡ ነው።
ዓለም አቀፍ የዜና ተቋም የሆነው ብሉምበርግ አሜሪካ ለሚገኙ ሠራተኞቹ ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ወጪ ለመደጎም በማሰብ በየቀኑ 75 ዶላር መስጠት ጀምሯል። የዩናይትድ ኪንግደም አማካሪ ድርጀት 'ፒደብልዩሲ' በበኩሉ በሕዝብ ትራንስፖርት ለሚንቀሳቀሱ ሠራተኞቹ 1 ሺ ፓውንድ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ታዋቂው የአሜሪካ ባንክ ጎልድማን ሳክስ ደግሞ ለሠራተኞቹ ነጻ ቁርስና ምሳ እንደሚያቀርብላቸው ተናግሯል። ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች በጣም ጥቂት ናቸው። ሚሊየኖችን የሚቀጥሩ ዓለም አቀፍም ሆነ የመንግሥት ድርጅቶች ያለ ምንም ድጎማ ነው ሠራተኞቻቸው ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ እያደረጉ ያሉት።
በለንደን የሚገኝ እና በሕግ ዘርፍ የሚሰራ አንድ ኩባንያም ቢሆን ሠራተኞች በቋሚነት ከቤት የሚሰሩበትን አማራጭ ይፋ አድርጓል። ሆኖም ይህንን አማራጭ የሚወስዱ ሠራተኞች ሙሉ ደመወዛቸውን አያገኙም። ድርጅቱ ያስቀመጠውን በቋሚነት ከቤት የመስራት አማራጭ የሚፈልጉ ሰዎች ከደመወዛቸው 20 በመቶው ይቆረጣል።
ከወረርሽኙ በፊት ሰዎች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ተጠምደው ስለሚውሉ መሰል ነገሮችን አያስተውሉም ነበር። አሁን ግን ሌላ አማራጭ እንዳለ ታይቷል።
ወረርሽኙ ከሁለት ዓመታት በፊት ዓለምን ሲያስደነግጥና የበርካቶችን አኗኗር እንዲሁም የሥራ ሁኔታ ሲቀያይር ሰዎች መልመድ አቅቷቸው ተቸግረው ነበር።
ከአካላዊ ርቀት መጠበቅ እስከ ማስክ ማድረግ፤ ከወዳጅ ዘመድ ጋር መሰባሰብ ክልከላ እስከ ምግብ ቤቶች መዘጋት አይነት አዳዲስ ሕጎች በርካቶችን ግራ ያጋባ ነበር። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ከቤት መስራት የሚለው ሀሳብ መጣ። ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ከቤት ሆኖ መስራት እንዴት ይቻላል? ብለው ተቃውመውትም ነበር። ነገር ግን አዲሱ የህይወት ዘይቤ ወራት ቢፈጅም ተለምዷል።
አሁን ላይ ደግሞ ከቤት ሥራችሁን መስራት አቁሙና ወደ ቢሮ ተመለሱ ሲባሉ ሰዎች አዲስ ሆኖባቸዋል።
ዮናስ እንደሚለው ለሁለት ዓመት ከለመደው የኑሮና የሥራ ዘይቤ ወደ ቀደመው ሕይወቱ መመለስ በጣም አስቸግሮታል። እሱ የሚሰራበት ድርጀትም ቢሆን ነገሮችን ተረድቶ ድጎማም ሆነ የደሞዝ ጭማሪ አላደረገም።













