መሪዋን ከቀናት በፊት በድምጽ ብልጫ ያነሳችው ፓኪስታን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መረጠች

ታትሟል

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን እሁድ ዕለት ያለመተማመን ድምጽ [አንድ በሥልጣን ላይ ያለ ግለሰብ በኃላፊነቱ ለመቀጠል ብቁ ነው ወይስ አይደለም በሚል የሚሰጥ ድምጽ] ብልጫ ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ የፓኪስታን ፓርላማ ሼህባዝ ሻሪፍን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መረጠ።

ካንን ከሥልጣን ለማውረድ ሲሰሩ የነበሩ የተቃዋሚዎች ጥምረት መሪ የፓርላማውን አብላጫ ድጋፍ ማግኘት ችለዋል።

በመሆኑም ሼህባዝ ሻሪፍ ነሐሴ 2023 ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ሥልጣን ላይ የሚቆይ አዲስ መንግሥት ይመሰርታሉ።

የ69 ዓመቱ ካን ከሥልጣናቸው የተነሱት ቀናትን ካስቆጠረና ከብዙ የፖለቲካ ድራማ በኋላ አነስተኛ ድምጽ በማግኘት ነበር።

ካን ከዚህ ቀደም ፓርላማውን በመበተን እና በአስቸኳይ ምርጫ እንዲካሄድ በመጠየቅ በእርሳቸው ላይ ሊካሄድ የነበረውን ያለመተማመን ድምጽ አሰጣጥ እንዲዘገይ ሙከራ አድርገው ነበር።

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድርጊቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በማለት የተቃዋሚዎችን አቤቱታ በማጽደቅ ያለመተማመን ድምጽ አሰጣጡ እንዲቀጥል አዝዟል።

በመሆኑም ሰኞ ዕለት ሻሪፍ ያለምንም ተቀናቃኝ በፓርላማው የተመረጡ ሲሆን የፓኪስታን 23ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።

የተቀናቃኝ እጩ ሸህ ማህሙድ ቁረይሺ በካን የሚመራው የፓኪስታን 'ተህሪክ ኢ ኢንሳፍ' ፓርቲ የፓርላማውን ድምጽ እንደማይቀበለው በመግለጽ አዳራሹን ጥሎ መውጣቱን አስታውቀዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፓርቲያቸው አብዛኞቹ የምክርቤት አባላት ከድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ቀደም ብሎ ከምክር ቤት አባልነታቸው ለቀዋል።