የእንግሊዝ ትልልቅ ሬስቶራንቶች ምግቦቻቸው የያዙትን ካሎሪ ይፋ ማድረግ ሊጀምሩ ነው

ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እንግሊዝ ውስጥ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ምግብ ቤት የሚያቀኑ ሰዎች በሜኑ (የምግብ እና የዋጋ ዝርዝር ማቅረቢያ) ላይ እያንዳንዱ ምግብ ያለውን ካሎሪ ማግኘት ይችላሉ።

በመሆኑም ከ250 በላይ ሠራተኞች ያሏቸው ምግብ ቤቶችና ካፍቴሪያዎች የሚያዘጋጇቸው ምግቦች ውስጥ ምን ያህል ካሎሪ እንዳለ በሜኑዎቻቸውና በድረ ገጻቸው ላይ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።

አዲሱ ሕግ ሰዎች ጤናማ ምርጫ በማድረግ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቋቋም መንግሥት ያወጣው ዕቅድ አካል ነው።

አንዳንድ ምግብ ቤቶች ሕጉ ወጪያችንን ይጨምራል ብለው ሰግተዋል። በአመጋገብ ችግር ላይ የሚሠራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ሕጉ ለጎጂ አስተሳሰቦች እና ባህሪያት አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሏል።

ሕጉ ምን አዲስ ነገር አለው?

በአዲሱ ሕግ መሠረት በእንግሊዝ የሚገኙ 250 እና ከዚያ በላይ ሠራተኞች ያሏቸው የምግብ እና የመጠጥ ቤቶች ቀድመው ካልተዘጋጁ ምግቦች እና ለስላሳ መጠጦች ውጭ የካሎሪ መረጃ ማሳየት አለባቸው።

እንደ ዌዘርስፑንስ ፐብስ እና የሪል ግሪክ ሬስቶራንት ያሉት ስለሚያበስሉት ምግብ የካሎሪ ይዘት መረጃ በሜኑዋቸው ላይ ያትማሉ። ማክዶናልድም ይህን ማድረግ ከጀመረ ከአስር ዓመታት በላይ ሆኖታል።

የሜክሲኮ ምግብ በማሰናዳት ስም ያተረፈው የዋሃካ መስራች ማርክ ሴልቢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅቱ ለደንበኞቹ በሚያቀርበው ምግብ እና መጠጥ መረጃ ላይ "ግልጽ ለመሆን ዝግጁ ነው" ብለዋል። ካሎሪንን በመለካት ላይ ያለው ትኩረት ችግር መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ይህ የታሪኩን አንድ ክፍል ብቻ ይነግረናል። የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለን የምናስበውን በምግብ ዙሪያ አንዳንድ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን ግን ይዘነጋል። ይህም በእርግጠኝነት ሊታሰብበት የሚገባ ይመስለኛል።" ብለዋል።

ሰዎች ዋሃካን የሚጎበኙት እንደ "ግብዣ" መሆኑን እንደሚያምኑ ሴልቢ ገልጸው ማንም ሜኑውን ከካሎሪ አንጻር እንደማይመለከተው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምግብ አብሳዮች በምግብ ቤቶች ውስጥ በየቀኑ የሚጠቀሙባቸውን 250 ግብአቶች በትክክል መጠቀማቸውን የሚያረጋግጥ አሠራር መፍጠር በንግዱ ላይ "በግልጽ ተጽእኖ በማሳደር ወጪውን ያንራል" ብለዋል።

ኩባንያው ለውጡን በመጠቀም እያንዳንዱ ምግብ የአየር ንብረት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመለካት ተጠቅሞበታል ብሏል።

የማስተርሼፍ ውድድር (የምግብ አብሳዮች ውድድር) አሸናፊው ስቬን-ሃንሰን ብሪት በትዊተር ገፃቸው ለውጡ "በኢንዱስትሪው ላይ የደረሰ አሰቃቂ ነገር ነው" ብሏል። ሕጉ "ፈጠራን፣ ልዩ መሆንን የሚያቆም እና ወደ አሰልቺ ምግብ የማብሰል አሠራር ሊያመራ ይችላል" ሲልም አስጠንቅቋል።

"ልጆች የሚያድጉት በሬስቶራንቶች፣ በሆቴሎች እና በካፌዎች ውስጥ ከምግቡ ስር ያለውን ትንሽ ቁጥር ብቻ በመመልከት ነው። ምርጫ የሚደረገው በቁጥር ላይ ተመርኩዞ ብቻ ነው። ጣዕም፣ ግብዓት፣ ታሪክ፣ የምግብ አሰራር ወይም የተመጣጠነ ምግብ ተፈላጊነት ይጠፋ እና ይሸፈናል። ትኩረቱም ወደ አዲስ አቅጣጫ ይዞራል" ብሏል።

የዩኬ ሆስፒታሊቲ ኃላፊ ኬት ኒኮልስ አዲሱ ሕግ "ሥራቸውን ለማስቀጠል ለሚታገሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ድርጅቶች በጣም በመጥፎ ጊዜ የመጣ ነው" ብለዋል።

"የካሎሪ መጠን ማሳወቂያ አተገባበር እንዲዘገይ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ጠይቀን ነበር። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ አስገዳጅ እንዳይሆን እና የተወሰነ የማስተንፈሻ ጊዜ ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።

"በኮቪድ ምክንያት ባለፉት 24 ወራት የተንገዳገዱ ድርጅቶች ኪሳራቸውን እንዲመልሱ የሚጠበቁ ንግዶች ውስብስብ እና ውድ የሆኑ አዲስ መረጃ በድንገት እንዲያስተዋውቁ መጠበቅ በጣም አሳሳቢ ነው።" ብለዋል ኬት ኒኮልስ

ተመጋቢዎችስ ምን ይላሉ?

ቻርሎት ሮበርትስ ለተባለችው የማክልስፊልድ ነዋሪ ለውጡ በምግብ ምርጫዋ ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም።

"ወደ ሬስቶራንቱ የመጣሁት መብላት የምፈልገውን አውቄ ነው። ጥሩ ምግብ እንደሚሆን እያወቅኩ ወደዚያ እሄዳለሁ። መብላት የምፈልገውን ብቻ ነው የምበላው" ትላለች የ19 ዓመቷ ወጣት።

የለንደን ነዋሪው ጄምስ ሃውለትም ለውጡ በምርጫው ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ተናግሯል። "መረጃዎቹን እንዳለሰፈሩ አላስተዋልኩም ነበር" ብሏል።

"በየትኛውም ቀን የሚሰማኝ ነው የሚሆነው። ፒዛ ከፈለግኩ ፒዛ እመገባለሁ። በርገር ካማረኝም በርገር አዛለሁ።"

ከሞንማውዝ ለመጡት የ57 ዓመቱ ፓትሪክ ካላጋን ግን እርምጃው በምግብ ምርጫቸው ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ይናገራሉ።

"ሰዎች ለሚመገቡት ነገር ትኩረት ይሰጣሉ ብዬ አስባለሁ። ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ሰዎች የበለጠ ንቁ የሆኑ ሲሆን ስለሚወስዱት ካሎሪም የማወቅ ፍላጎት አላቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የ56 ዓመቷ ኬት ካላጋን ሰዎች "ለምንበላው ነገር ራሳቸን ኃላፊነት መውሰድ አለብን" ሲሉ በሕጉ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የአመጋገብ ሥርዓት ችግር ላይ የሚሠራው ቢት የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚለው በምግብ ዝርዝር ውስጥ ካሎሪ መጥቀስ አስገዳጅ መደረጉ ለጎጂ የአመጋገብ ችግር አስተሳሰቦች እና ባህሪያት መባባስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ዳይሬክተር ቶም ኩዊን እንዳሉት የካሎሪ መረጃ በአመጋገብ ችግር የተጎዱ ሰዎች ላይ ጭንቀትና ድብርት እንደሚፈጥር የሚያሳይ ማስረጃ አለ።

"ሕጉ የሰዎችን የአመጋገብ ልማዶችን ስለመቀየሩ የሚያሳዩ ማስረጃዎች በጣም ውስን ናቸው" ብለዋል።

ቢት ለቢቢሲ እንደገለጸው በእንግሊዝ ብቻ 1.25 ሚሊዮን ሰዎች የአመጋገብ ችግር አለባቸው። መንግሥት በአመጋገብ ችግር በተጎዱ ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንዲያሰላስል እና "የአመጋገብ ችግር ባለሙያዎችን እንዲያማክር" ያለማቋረጥ መጠየቁን አስታውቋል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት አገሪቱ ካጋጠሟት የጤና ችግሮች አንዱ መሆኑን የጤና እና የማኅበራዊ እንክብካቤ ሚኒስቴር አስታውቋል። የምግብ ዝርዝር መገለጹ ሰዎች ጤናማ ምርጫ እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግሯል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አክለውም ሰዎች በሱፐር ማርኬቶች የሚሸጡ ምርቶችን የምግብ መረጃ ማየትን ተለማምደዋል ብለዋል።

መንግሥት ፖሊሲው በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን አስታውቋል። ከአዕምሮ ጤና በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ባለሙያዎች ጋር "በሰፊው" መምከሩንም ገልጿል።