ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን ለልጅ ልጃቸው ቤተ-መንግሥት ውስጥ ድል ያለ ሠርግ ሊደግሱ ነው
ፕሬዝደንት ጆ ባይደንና ቀዳማዊት እመቤቷ ለልጅ ልጃቸው ናዮሚ በነጩ ቤተ መንግሥት ድል ያለ ሠርግ ሊደግሱ ነው።
የ28 ዓመቷ ትልቋ የባይደን ልጅ ልጅ ናዮሚና የ24 ዓመቱ ዕጮኛዋ ፒተር ኒል በአሜሪካ ውዱ የሠርግ አዳራሽ ሊጋቡ ቀጠሮ ይዘዋል።
ባይደን፤ የልጅ ልጃቸው በአያቶቿ ክብር ይሰማታል ብለዋል።
የኮሎምቢያ ሕግ ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነችው ናዮሚ የሕግ ተማሪ ከሆነው ዕጮኛዋ ጋር ትዳር ልትመሠርት መሆኑን ለሕዝብ ያሳወቀችው ባለፈው መስከረም ነው።
ባይደን ዋይት ውስጥ ሠርግ ለማዘጋጀት ዱብ ዱብ ያሉ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት አይደሉም።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ፕሬዝደንት መቀመጫ በሆነው ዋይት ሃውስ የቀደሙ ፕሬዝደንቶች ሠርግ ደግሰዋል።
ጆ ባይደን በሚመጣው ኅዳር የልጅ ልጃቸውን ሠርገው ለመሸኘት ደፋ ቀና ላይ ናቸው።
ከዚህ በፊት በ2008 የጆርጅ ደብልዩ ልጅ ጄና ቡሽ ዋይት ሃውስ ውስጥ ዳስ ተጥሎ ተሠርጎላት ነበር።
ዋይት ሃውስም ለመጀመሪያ ጊዜ ሠርግ ያስተናገደው በፈረንጆቹ 1812 ነበር።
በወቅቱ ቀዳማዊት እመቤት የነበሩት ዶሊ ማዲሰን እህት ናቸው ዘመድ አዝማድ በተሰበሰበበት ያገቡት።
ከዚያ ቀጥሎ በ1874 የወቅቱ ፕሬዝደንት የነበሩት ዩሊሴስ ግራንት ልጃቸው ኔሊ ግራንትን የዘመኑን ድግሶች ባስናቀ ድግስ ሠርገው ሸኟት።
ኢስት ሩም የተባለው የዋይት ሃውስ ክፍል በነጭ አበባ ደምቆ ሙሽሪት ርዝመቱ አጀብ የሚያሰኝ የሠርግ ልብስ እየጎተተች ነበር ለሕዝቡ ሰላምታ እየሰጠች ያለፈችው።
ፕሬዝደንት ዩሌሲስና ቀዳማዊት እመቤታቸው የ19 ዓመት ልጃቸውን ብዙዎችን ባስቀና ድግስ ነው የዳሯት።
ፕሬዝደንት ግሮቨር ክሊቭላንድ ደግሞ ፕሬዝደንት ሳሉ በዋይት ሃውስ ጋብቻ ቀለበት ያጠለቁ ብቸኛው መሪ ናቸው።
ክሊቭላንድ በኋላ ቀዳማዊ እመቤት የሆኑት ፍራንሲስ ፎልሰንን 'ብሉ ሩም' በተሰኘው የዋይት ሃውስ ክፍል በተዘጋጀ እራት ነው ያገቧቸው።
የፕሬዝደንት ሊንደን ጆንሰን ልጅ ሊንዳ በርድ ጆንሰን እንዲሁም በ1967 ቻርልስ ሮብን ያገቡት በታላቁ ቤተ መንግሥት ነው።
በ1971 ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ልጃቸው ትሪሺያ ኒክሰንን ሮዝ ጋርደን በተሰኘው ውብ ሥፍራ ደግሰው ድረዋል።
ዋይት ሃውስ የአሜሪካ መሪዎች ልጃቸውን አሊያም የልጅ ልጃቸውን የሚድሩበት ብቻ ሳይሆን የመሥሪያቱ ቤቱ ሠራተኞችም ዕድሉን ካገኙ የሚሰርጉበት ነው።
በ2013 የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ፎቶ አንሺ የነበረው ፒተር ሱዛ በነጩ ቤተ መንግሥት ሠርጉን አድርጎ ነበር።