የአውሮፓ ሻምፒየኗ ጣሊያን ዳግም ለዓለም ዋንጫ ሳታልፍ ቀረች

ታትሟል

ሐሙስ ምሽት ከሰሜን መቂዶኒያ ጋር የተጋጠመችው የአውሮፓ እግር ኳስ ኃያሏ ጣሊያን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ተሸንፋ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሳታልፍ ቀርታለች።

የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ጣሊያን፤ ከዚህ ቀደም በሩሲያ አዘጋጅነት ተካሂዶ በነበረው የዓለም ዋንጫም ተሳታፊ አልነበረችም።

የሰሜን መቂዶኒያው አሌክሳንድር ትራሆቭስኪ መደበኛ የጨዋታው ሰዓት ተጠናቆ የመጨረሻ ጭማሪ ሰዓት ላይ በጣሊያን ተጫዋቾች የተሰራውን ስህተት በመጠቀም አስደናቂ ግብ በማስቆጠር ነው አገሩን አሸናፊ ማድረግ የቻለው።

92ኛው ደቂቃ ላይ ግቡ ሲቆጠር የሰሜን መቂዶኒያ ተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን እራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ደስታቸውን ሲገልጹ፣ በደጋፊዎቻቸው ፊት በሜዳቸው የተጫወቱት ጣሊያኖች በሐዘን ተንበርክከው መሬት ሲደበድቡ ታይተዋል።

ይህንን ተከትሎም የዓለም ዋንጫን አራት ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው ጣሊያን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫው እንደማትሳተፍ ተረጋግጧል።

በሮቤርቶ ማንቺኒ የሚመሩት 'አዙሪዎቹ' በሚል ቅጽል የሚታወቀው የጣሊያን ቡድን የ2020 የአውሮፓ ዋንጫን ሲያሸንፍ፣ ይህ ቡድን በዓለም ዋንጫውም ያልተጠበቁ በርካታ ድሎችን እንደሚያስመዘግብ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ነገር ግን ሐሙስ ዕለት የሰሜን መቂዶኒያን ግብ መድፈር አቅቷቸው በሽንፈት ከቀጣዩ የአለም ዋንጫ ውጪ ሆነዋል።

በዓለም እግር ኳስ ደረጃ 67ኛ ላይ የተቀመጡት ሰሜን መቂዶኒያዎች 6ኛ ላይ የምትገኘው ጣሊያንን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከወሳኝ 90 ደቂቃዎች በኋላ በዓለም ዋንጫው መሳተፍ አለመሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ።

ቀጣይ የመጨረሻ ተጋጣሚያቸው ደግሞ የክርስቲያኖ ሮናልዶ አገር ፖርቹጋል ነች።

ምንም እንኳ በርካቶች ጣሊያን ይህንን ጨዋታ በቀላሉ አሸንፋ ከፖርቹጋል ጋር የሚኖረው ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል ብለው ቢገምቱም፣ የእግር ኳስ ነገር ሆኖ ጣሊያን በደጋፊዎቿ ፊት አምስት ጊዜ ብቻ ወደ ግብ ሙከራ በማድረግ ያልተጠበቀ ሽንፈትን አስተናግዳለች።

የሰሜን መቂዶኒያ ቀጣይ ተጋጣሚ ፖርቹጋል ደግሞ ሐሙስ ምሽት ከቱርክ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።

ፖርቹጋል የዓለም ዋንጫ ተስፋዋን በእጅጉ ያለመለመውን ድል ስታስመዘግብ በቀላሉ አልነበረም። ምንም እንኳን ፖርቹጋሎች በኦታቪዮ እና በዲዮጎ ጆታ ግቦች ሁለት ለባዶ መምራት ቢችሉም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 25 ደቂቃዎች ሲቀሩት የቱርኩ ቡራክ ዪማዝ ግብ አስቆጥሮ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል።

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ቱርክ የፍጹም ቅጣት ምት ያገኘች ቢሆንም የመጀመሪያዋን ግብ በማስቆጠር ደጋፊዎቹን ያስፈነጠዘው ቡራክ ዪማዝ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ቱርካውያን አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል የግብ ዕድል ባገኙ ጊዜ በደስታ ቢጨፍሩም አጥቂው ግን ኳሷን ከግቡ ከአግዳሚ በላይ በመጠለዝ አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል።

የፍጹም ቅጣት ምቱ ወደ ግብነት አለመቀየሩ ያነቃቃቸው ፖርቹጋሎች አጥቅተው መጫወት በመጀመር በፈርናንዶ ኑኔዝ አማካይነት ሦስተኛ ግብ አስቆጠሩ። ፖርቹጋሎች ቀጣይ ተጋጣሚያቸውን ሲያውቁ ደግሞ ይበልጥ ደስታ ሆኖላቸዋል።

ምክንያቱም ፖርቹጋሎችን ጨምሮ ሁሉም ደጋፊ ጣሊያን እንደምታሸንፍና ቀጣይ ተጋጣሚዎቻቸው አዙሪዎቹ እንደሚሆኑ ነበር የገመቱት። ነገር ግን ባልተጠበቀ መልኩ ሰሜን መቂዶኒያ ጣልያንን ማሸነፏን ተከትሎ የፖርቹጋል የመጨረሻ ተጋጣሚ ሆናለች።

''እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች በጣም ፈታኝ ናቸው። የመጀመሪያውን ፈተና አልፈናል። አሁን ሙሉ ትኩረታችን ቀጣዩ ጨዋታ ላይ ነው። ሰሜን መቂዶኒያ ጣሊያንን አሸንፋለች። ጣሊያንን ካሸነፉ ደግሞ እኛን እንዴት ሊከብዱን እንደሚችሉ እናውቃለን'' ብለዋል የፖርቹጋሉ አሰልጣኝ ሳንቶስ።

በሌሎች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ስዊድን ቼክ ሪፐብሊክን አንድ ለባዶ ያሸነፈች ሲሆን ዌልስ ኦስትሪያን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችላለች።

የሩሲያን ከውድድሩ መታገድ ተከትሎ በቀጥታ ወደ መጨረሻው ዙር ያለፈችው ፖላንድ በቀጣይ ከስዊድን ትፋለማለች። ከሁለቱ አሸናፊው ቡድን ደግሞ በኳታር የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናል ማለት ነው።

ስኮትላንድና ዩክሬን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሰኔ መዘዋወሩን ተከትሎ ኦስትሪያን ያሸነፈችው ዌልስ ተጋጣሚዋን ለማወቅ ለወራት መጠበቅ አለባት።