ሱዳን በግዛቷ ውስጥ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች የሉም ስትል አስተባበለች

ታትሟል

ከሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያዎች የመጡ ቅጥረኛ ወታደሮች በግዛቷ ውስጥ አለመኖራቸውን ሱዳን አስተባበለች።

የሱዳን መንግሥት ማስተባበያውን ያወጣው የብሪታኒያ፣ የአሜሪካ እና የኖርዌይ መልዕክተኞች ዋግነር የተባለው ወታደራዊ ተቋም በሱዳን ውስጥ በተለያዩ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል በማለት የጋር መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

የምዕራብ አገራት መልዕክተኞቹ እንደሚሉት ቡድኑ በሱዳን ውስጥ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት እና በሕገ ወጥ የወርቅ ቁፋሮ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል ብለው ይከሱታል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለዚህ ክስ በሰጠው ምላሽ "መንግሥት ይህንን ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ያደርገዋል" በማለት አስተባብሏል።

የሱዳን ባለሥልጣናት ምዕራባውያኑን ዲፕሎማቶች አገራቸውን እየተካሄደ ካለው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ጋር ለማያያዝ ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

በቅርቡ የሱዳን ምክትል መሪ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን "ሄሜቲ" ወደ ሞስኮ ተጉዘው ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በአፍሪካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ተብለው ሲከሰሱ ነበር።

ምዕራባውያን አገራት የሩሲያው የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ማሊ ውስጥ ተሰማርተው እንደነበር ሲገልጹ ቆይተዋል።

ወታደራዊው ቡድን ሊቢያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህ ቅጥረኛ ወታደሮች ትሪፖሊ ውስጥ የሚገኘውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውን የሊቢያ መንግሥትን የሚወጉትን አፈንጋጩን ጄነራል ኻሊፋ ሐፍጣርን በመደገፍ ሲዋጉ ቆይተዋል።

የሱዳን የረጅም ጊዜ አምባገነን መሪና የሩሲያ ወዳጅ የነበሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወደ መሪነት የመጡት የአገሪቱ ወታደራዊ መሪዎች ከሞስኮ ጋር ግንኙነታቸውን ቀጥለዋል።

አል ባሽር ከሥልጣን ከመወገዳቸው ከጥቂት ዓመታት በፊት በጥቁር ባሕር የመዝናኛ ከተማ ሶቺ ውስጥ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተገናኙበት ጊዜ "ከአሜሪካ ከሚሰነዘርባት የጠብ አጫሪነት ድርጊት" ሩሲያ እንድትከላከላት ጠይቀው ነበር።