በካናዳ መስጊድ ውስጥ መጥረቢያ ይዞ ጥቃት ሊፈጽም የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Google
በካናዳ አንድ መስጊድ ውስጥ የሚገኙ አማኞች ቅዳሜ ዕለት ጠዋት ሰላት ላይ ሳሉ መጥረቢያ ይዞ የሚያቃጥል ፈሳሽ በመርጨት ጥቃት ሲፈፅም የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው ምዕመናኑ ከግለሰቡ ጋር ግብ ግብ ገጥመው ይዘው ካቆዩት በኋላ ነው።
አንድ ምዕመን ከግለሰቡ እጅ ላይ መጥረቢያውን በመቀማት ፖሊስ በስፍራው እስከሚደርስ ድረስ እንዳይንቀሳቀስ መሬት ላይ አስተኝቶ ይዞት እንደቆየ የካናዳ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ድርጊቱን የፈፀመው የ24 ዓመቱ ግለሰብ በሚሲሳውጋ ከተማ ዳርቻ ላይ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ ተመስርቶበታል።
ግለሰቡ በረጨው ፈሳሽ አንዳንድ ምዕመናን ጉዳት እንደደረሰባቸው የመስጊዱ ኢማም ተናግረዋል።
ከምዕመናኑ መካከል አንዱ አጋጣሚውን "አስፈሪ" ሲል የገለፀው ሲሆን ግለሰቡ በእጁ መጥረቢያ ይዞ እና ከበርበሬ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሚያቃጥል ፈሳሽ ሦስት ሰዎች ላይ ሲረጭ ከመመልከቱ በፊት ጩኸት መስማቱን ገልጿል።
"በወቅቱ ግለሰቡ ፈሳሹን ሲረጭ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የነበሩ ሰዎች አንድ ነገር እንደተፈጠረ ተረዱ። ከዚያም ከወጣት ወንዶቹ መካከል አንዱ ግብ ግብ ገጥሞ ግለሰቡ በያዘው መጥረቢያ ጥቃት መፈፀም ሳይጀምር ከእጁ ላይ ቀማው" ሲል ኑራኒ ሴራሊ ለካናዳው ጋዜጣ ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።
ከዚያም ወጣቱ ፖሊስ በስፍራው እስከሚደርስ ድረስ ግለሰቡን ይዞ እንዳቆየው ኑራኒ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የመስጊዱ ኢማም ኢብራሒም ሂንዲም በሰጡት መገለጫ ግለሰቡ ወደ ሥፍራው የገባበትን ቅጽበት ሲገልጹ "በየትኛውም ምዕመን ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በርካታ ምዕመናን ድርጊቱን በጀግንነት ሊያስቆሙት ችለዋል" ብለዋል።
"የእኛ ማኅበረሰብ መቼም አይሰበርም፤ ጥቃትን እምቢ ብለናል" ሲሉ ኢማም ኢብራሒም አክለዋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለውን ግለሰብ ስም ሞሐመድ ሞይዝ ኦማር እንደሚባል ይፋ አድርጓል።
በዚህ ግለሰብም ላይ ሕይወትን ለአደጋ በማጋለጥ ወይም በመሣሪያ አካል ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ እና አደገኛ ንጥረ ነገር መጠቀምን ጨምሮ በስድስት ወንጀሎች ክስ መስርቶበታል።
መጀመሪያ ላይ ግለሰቡ ድርጊቱን ለምን እንደፈፀመው እርግጠኛ መሆን ባይቻልም አሁን ላይ መርማሪዎች "በጥላቻ በመነሳሳት" የተፈጠረ ክስተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ ድርጊቱን ካወገዙ የካናዳ እውቅ ሰዎች አንዱ ሲሆኑ ይህ ጥቃት "የሚሰቀጥጥ ነው" በማለትም በመስጊዱ ውስጥ የነበሩ ምዕመናንን ድፍረት አድንቀዋል።
የካናዳ ሙስሊም ማኅበረሰብ እአአ በ2017 ስድስት ሰዎችን የገደለውንና ሌሎች 8 ሰዎችን ለጉዳት የዳረገውን የኪዩቤክ ከተማ መስጊድ ጥቃትን ጨምሮ ለበርካታ ጊዜ ጥቃቶች ደርሰውበታል።
ባለፈው ዓመትም በኦንታሪዮ ውስጥ አራት የአንድ ሙስሊም ቤተሰብ አባላት በአንድ ተሽከርካሪ ተገጭተው ተገድለዋል። ፖሊስ ይህንን ጥቃት "ሆነ ተብሎ የተፈፀመ እስላማዊ የጥላቻ ጥቃት" ሲል ገልጾታል።












