ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ መኖሪያ ቤቶችን እየሰበረ ምግብ የሚሰርቀው ግዙፍ ድብ በፖሊስ እየታደነ ነው
በአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት በርካታ መኖሪያ ቤቶች ሰብሮ እየገባ የሰዎች ምግብ የሚበላው ግዙፍ ድብ በፖሊስ እየታደነ ነው።
'ሄንክ ዘ ታንክ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ግዙፍ ጥቁር ድብ 227 ኪሎ ግራም ይመዝናል ተብሏል።
የግዛቲቱ ባለሥልጣናት ይህ ድብ ሰዎች የሚመገቡትን ምግብ መመገብ በመልመዱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ40 ያላነሱ ቤቶችን ሰብሮ ገብቷል። ሄንክ ዘ ታንክ በአንዳንድ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።
"ጉልበቱን እና ግዝፈቱን ተጠቅሞ መኖሪያ ቤቶችን ሰብሮ መግባት ልማዱ አድርጎታል" ሲሉ የካሊፎርኒያ ግዛት የአሳ እና የዱር እንስሳት ቢሮ ቃል አቀባይ ፒተር ቲራ ተናግረዋል። ይህ ድብ "በሮችንና መስኮቶችን ገንጥሎ ይገባል" ሲሉ ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።
ከመደበኛ የድብ መጠን እጅግ የሚገዝፈው ሄንክ በመጠኑ እና በቀለሙ በሰዎች በቀላሉ እንደሚለይ ተገልጿል።
ሰዎች ድቦችን ለማባረር የሚጠቀሙባቸው ገዳይ ያልሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ንዝረት የሚያወጡ መሳሪያዎች እና ከፍተኛ ድምጽ የሚያወጡ ማይክራፎኖች ይህን ድብ ለማባረር ውጤታማ አልሆኑም።
ይህ ድብ እንደተቀሩት ዝርያዎቹ የዱር ፍሬዎችን ከመብላት ይልቅ የፒዛ እና የአይስ ክሬም ትርፍራፊን መመገብ እንደሚመርጥ የአካባቢው ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።
የዱር እንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች ድቡ እንዳይገደል እና ወደ ሌላ የእንስሳት ማቆያ ስፍራ እንዲዘዋወር እየጠየቁ ይገኛሉ።