ንግሥት ኤልዛቤት በተደረገላቸው ምርመራ ኮቪድ ተገኘባቸው

ታትሟል

ንግሥት ኤልዛቤት በተደረገላቸው ምርመራ ኮቪድ እንደተገኘባቸው የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስታወቀ።

ንግሥቲቱ "ቀላል ጉንፋን መሰል ምልክቶች" እንደታዩባቸውና "ቀለል ያሉ ሥራዎችን እያከናወኑ" በዊንድሰር መኖሪያቸው ቀጣዩን ሳምንት እንደሚያሳልፉ ከቤተ መንግሥታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

"አስፈላጊውን መመሪያዎች በመከተል የህክምና ክትትላቸውን ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ" ብሏል መግለጫው ጨምሮ።

የ95 ዓመቷ ንግሥት ባለፈው ሳምንት ኮቪድ ከተገኘበት ታላቅ ልጃቸውና የንግሥናቸው ወራሽ ከሆነው ልጃቸው ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተነግሯል።

ንግሥቲቱ ከሚኖሩበት ዊንድሰር ቤተ መንግሥት ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎችም ወረርሽኙ እንደተገኘባቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

ንግሥት ኤልዛቤት ኮቪድ እንደተገኘባቸው የተገለጸው በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ በንግሥና መንበር ላይ 70 ዓመት በመቆየት የመጀመሪያዋ መሆናቸው ከተከበረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።

ንግሥቲቱ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባታቸውን ባለፈው ዓመት ጥር ላይ የወሰዱ ሲሆን ከዚያ በኋላም ሁለተኛውን እንደተወጉ ይታመናል።

ንግሥት ኤልዛቤት ቀደም ሲል ቫይረሱ መያዛቸው ከተገለጸው ልዑል ቻርለስ ጋር ንክኪ እንዳላቸው ከተገለጸ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ እራሳቸውን አግልለው ቆይተው ነበር።

የልዑል ቻልርለስ ባለቤትም ከቀናት በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው ታውቋል። ልዑሉ በወረርሽኙ የተያዙት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ባለቤታቸው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ንጉሣዊው ቤተሰብ የራሱ የሆነ ሐኪሞች ያሉት ሲሆን፣ በለንደኑ ሴንት ማሪስ ሆስፒታል የሚሰሩትና በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሰር ሁው ቶማስ የንግሥቲቱ ሐኪም ናቸው።