ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ'ኤል ቻፖ' ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉት የሆንዱራስ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
የሆንዱራስ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሁዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ክስ ምክንያት በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዝደንት ከሃገር እንዳይወጡ በማድረግ ተላልፎ እንዲሰጣት ከጠየቀች ከሰዓታት በኋላ ፖሊስ ዋና ከተማዋ ቴጉሲጋልፓ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተሰማርቷል።
የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላ የቀድሞ ፕሬዝደንት በመኖሪያ ቤታቸው በመቆየት እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል። ሄርናንዴዝ በካቴና ታስረው ከመኖሪያ ቤታቸው ሲወሰዱም ታይቷል።
ሄርናንዴዝ እስከ እአአ 2014 ድረስ ሆንዱራስን በመሪነት ያስተዳደሩ ሲሆን አሁን ላይ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ ውስጥ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ታናሽ ወንድማቸው ቶኒ ሄርናንዴዝ በሚገኝበት በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ሰንሰለት ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው ተከስሰዋል።
የቶኒ ሄርናንዴዝ ችሎት በተሰማበት ወቅት አቃብያነ ህጎች ታዋቂው የሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ጆአኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን በግሉ ለቶኒ ሄርናንዴዝ አንድ ሚሊየን ዶላር ሰጥቷል ሲሉ ከስሰው ነበር።
እንደ አቃቤ ህግ ገለጻ ከሆነ "ኤል ቻፖ" ጉዝማን ገንዘቡን ለወንድሙ ጁዋን ኦርላንዶ እንደ ጉቦ እንዲሰጠው ነግሮታል።
ሆንዱራስ ለዓመታት ከደቡብ አሜሪካ ወደ አሜሪካ ለሚገቡ ዕጾች መሸጋገሪያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኮኬይን የሚመረትባት አገር ሆናለች።
ሁዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመዋጋት የተቻላቸውን ሁሉ እንዳደረጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመንም የአሜሪካ መንግስትን ድጋፍ ሲያገኙ ቆይተዋል።
በኋላም በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዘመን ከአሜሪካ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻክሯል።
ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ሄርናንዴዝ በሙስና ወንጀል ምክንያት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከተከለከሉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካቷቸዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ የቀድሞው የሆንዱራስ መሪ የሙስና እና የአደንዛዥ ዕፅ ዘውውር ተግባራትን በመፈጸም ወይም በማመቻቸት ከፍተኛ ሙስና ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል። ከህገወጥ ተግባር የሚገኘውን ገንዘብ ለፖለቲካ ዘመቻ እንደተጠቀሙበት የሚገልጹት ሪፖርቶችም ተአማኒነት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
የተፈረደባቸው የዕፅ አዘዋዋሪዎች በሰጡት መግለጫ ላይ ተመስርቶ እየተከሰሱ መሆኑን በመጥቀስ ሄርናንዴዝ ለብሊንከን ምላሽ ሰጥተዋል።
የማዕከላዊ አሜሪካ ፓርላማ አባል በመሆናቸው ያለመከሰሰ መብት አላቸው ሲሉ ጠበቃቸው ተከራክረዋል።
የተሰጣቸው ያለመከሰስ መብት በአገሪቱ መንግሥት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።