በፓኪስታን በነፍሰ ጡር ጭንቅላት ሚስማር የሰካው 'ባህላዊ ፈዋሽ' በፖሊስ እየተፈለገ ነው

ታትሟል

ፓኪስታን ውስጥ በአንድ ነፍሰ ጡር ጭንቅላት ላይ ሚስማር የሰካው ባህላዊ 'ሐኪም' በፖሊስ እየተፈለገ ይገኛል።

ነፍሰ ጡሯ አምስት ሴንቲ ሜትር ጠልቆ አናቷን የበሳውን ሚስማር በጉጠት ለማውጣት ሞክራ እምቢ ሲላት ፐሻዋር ግዛት የሚገኝ ሆስፒታል ሄዳለች።

መጀመሪያ ላይ ሚስማሩን ጭንቅላቷ ውስጥ ያስገባችው እራሷ እንደሆነች ተናግራ ነበር። ኋላ ላይ ግን አንድ እምነትን መሠረት ያደረገ ፈዋሽ 'ወንድ እንድትወልጂ' ሲል ሚስማሩን እንደሰካባት ገልጻለች።

ፖሊሶች ጉዳዩን እየመረመሩ ሲሆን፤ የጭንቅላቷ የኤክስ-ሬይ ምስል በበይነ መረብ ተለቋል።

ሌዲ ሪዲንግ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩት ዶ/ር ሒዳር ካሐን "ራሷን ባትስትም ከባድ ስቃይ ውስጥ ነበረች" ብለዋል።

ስለ ባህል ፈዋሹ ከጎረቤቶቿ ከሰማች በኋላ እንደሄደች የሆስፒታል ሠራተኞችን ጠቅሶ ዳውን ጋዜጣ ዘግቧል።

ሦስት ሴት ልጆች እንዳሏትና አራተኛ ሴት ከወለደች ባሏ ጥሏት እንደሚሄድ እንዳስፈራራትም ተገልጿል።

"የሦስት ወር ነፍሰ ጡር ናት። ባሏ ስላስፈራራት ነው ወደ ባህላዊ ፈዋሹ የሄደችው" ብለዋል የሆስፒታሉ ሠራተኞች።

በአንዳንድ የደቡብ እስያ አካባቢዎች ወንድ ልጅ መውለድ ይመረጣል። ወንድ ልጅ አድጎ ለቤተሰቡ ገንዘብ እንደሚያመጣም ይታመናል።

ይህ አስተሳሰብ ብዙ እምነትን ያማከሉ 'ፈዋሾች' ፈጥሯል።

ፓኪስታን ውስጥ ባህላዊ ፈዋሽ የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ በሰሜን ምዕራብ ፓሊስታን የሚሠሩ ፈዋሾች የእስልምና አስተምህሮትን ተመርኩዘው ያክማሉ።

ድርጊታቸው ግን በበርካታ የእስልምና ተከታዮች ተወግዟል።

የፐሻወር ፖሊስ ኃላፊ አባስ አህሳን ልዩ ቡድን ተቋቁሞ 'ፈዋሹ' እየተፈለገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

"ይህንን ውሸታም ፈዋሽ ለፍትሕ እናቀርበዋለን። በዚች ሴት ሕይወት ቀልዷል። በሐሰተኛ እምነት ጭንቅላቷ ውስጥ ሚስማር ሰክቷል" ብለዋል ኃላፊው።

ፖሊሶች ነፍሰ ጡሯ የታከመችበት ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ለምን ክስተቱን ለፖሊስ ሪፖርት እንዳላደረጉ እየጠየቁ ነው።

ሚስማሩ ከጭንቅላቷ ከወጣላት በኋላ ከሆስፒታሉ የወጣችውን ነፍሰ ጡር ለማግኘትም እየሞከሩ ይገኛሉ።

በነፍሰ ጡሯ ጥቆማ 'ፈዋሹን' በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

የፖሊስ ኃላፊው "በቅርቡ እጃችን ይገባል" ብለዋል።