ከከረዩ የገዳ አባላት ግድያ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች መያዙን የኦሮሚያ ፖሊስ አስታወቀ

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን

የፎቶው ባለመብት, Oromia Comm Bureau

የምስሉ መግለጫ, የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን
ታትሟል

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከከረዩ የገዳ አባላት ግድያ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

ሐሙስ ጥር 26/2014 ዓ.ም. የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ከግድያው ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ስለማለታቸው የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

በዚህ ዓመት ኅዳር መጨረሻ ላይ የከረዩ አባ ገዳን ጨምሮ 14 የከረዩ የገዳ አባላት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለመገደላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸው ይታወሳል።

የገዳ አባላቱን ግድያ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረገውን ምርመራ መሠረት በማድረግ ባወጣው ሪፖርት፤ የከረዩ የገዳ አባላት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ስለመገደላቸው አመላክቶ ነበር።

ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ግርማ ገላን በመግለጫቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች የክልሉ ፖሊስ አባላት ስለመሆናቸው ሆነ ስለማንነታቸው ያሉት ነገር የለም።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ተከትሎ ባሰፈረው ምክረ ሃሳብ ላይ በገዳ አባላቱ ከሕግ ውጪ ግድያ ላይ ተሳትፎ ያላቸው በሕግ እንዲጠየቁ ጥያቄ አቅርቧል።

ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው የኢሰመኮን ሪፖርት የክልሉ ፖሊስ ስለመቀበሉም ሆነ ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ሪፖርቱን ተከትሎ ስለመሆኑ ያሉት ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ኮሚሽነር ግርማ ገላን በግድያው "እጁ ያለበት የትኛውም አካል ለፍርድ ይቀርባል" ያሉ ሲሆን የወንጀል ምርመራው በዝርዝር ተከናውኖ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ

ኮሚሽኑ በግድያ ዙሪያ በሰበሰባቸው እና አገናዘብኳቸው ባላቸው ማስረጃዎች መሰረት 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደውና የአካባቢ የአስተዳደር ሰዎች ባሉበት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በጥይት ተመተው የተገድለዋል ብሏል።

ይህም ግድያ ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ እንዳገኘው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ሪፖርኡ አክሎም ለዚህ ግድያ እንደምክንያት የሚጠቀሰው የገዳ አባላቱ ከመገደላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ኅዳር 21/2014 ዓ.ም. ከክልል፣ ከዞን እና ከፈንታሌ ወረዳ የተወጣጡ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች በመሄድ ውይይትና ቅኝት አድርገው ነበር።

ከዚህ በኋላ የፀጥታ ኃይሉ አባላት ከአካባቢው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት 11 የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውን እና በዘጠን አባላት ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሶ እንደነበረ በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

አስራ አንዱ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በተገደሉ በቀጣይ ቀን ኅዳር 22/2014 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ ከ100 ያላነሱ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና የመደበኛ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች የገዳ አባላቱ ሰፍረው ወደሚገኙበት ቦታ መሄዳቸውን የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ መናገራቸው ተጠቅሷል።

የፖሊስ አባላቱ በቦታው እንደደረሱ ቤት ለቤት በመዞር በአካባቢው የነበሩ 39 ወንድ የገዳ አባላትን ትጥቅ አስፈትተው በአንድ ቦታ እንደሰበሰቡ ነዋሪዎች ለኢሰመኮ መርማሪ ቡድኑ አስረድተዋል።

በመቀጠልም የፀጥታ ኃይል አባላቱ የያዟቸው 39 ሰዎች ሰዎችን በጭነት መኪና ላይ ከነበሩበት ቦታ ርቆ ወደሚገኝ ስፍራ ይዘው ሄደዋል።

በፀጥታ ኃይሎቹ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች በሁለት ቡድን እንዲከፍሉ ተደርገው፤ አባ ገዳ ከድር ሀዋስን ጨምሮ 16 ዋና ዋና የገዳ አባላት በአንድ ቦታ እንዲሆኑ ቀሪዎቹ 23 ሰዎች ደግሞ በመኪና ተጭነው ወደ ሌላ ስፍራ መወሰዳቸውን ለኮሚሸኑ ቃላቸውን የሰጡ የዓይን እማኝ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ኢሰመኮ አባ ገዳ ከድር ሀዋስን ጨምሮ በስም የተጠቀሱ 14 ሰዎች በሆዳቸው እንዲተኙ ከተደረጉ በኋላ መገደላቸውን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ ከተኙበት ተነስተው ወደ ጫካ በመሮጥ እየተተኮሰባቸው ማምለጣቸውን ገልጸዋል ይላል።

የመንግሥት ምላሽ

በከረዩ ገዳ አባላት ላይ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የክልሉ መንግሥት እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም መንግሥት 'ሸኔ' ሲል የሚጠራውን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ኮሚሽኑ የክልሉን መንግሥት ምላሽ ለማካተት ለክልሉ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በደብዳቤ ቢጠይቅም ሁለቱም የክልሉ መሥሪያ ቤቶች ምላሽ አለመስጠታቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።

የፀጥታ ኃይሎቹ ግድያውን ከሕግ ውጪ ፈጽመዋል ተብሎ የተከሰሰው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ይህንን የኮሚሽኑን ሪፖርት በተመለከተ አስካሁን የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም።