ሰሜን ኮሪያ በሚሳኤሎች ተነስተዋል ያለቻቸውን ምስሎች ይፋ አደረገች

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ አገሪቱ ካስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በአንዱ ተነስቷል ያለችውን ምስል ይፋ አደረገች።

በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ይፋ የተደረገው ይህ ምስል የኮርያ ባሕረ ገብን እና አካባቢውን ያሳያል።

ሰሜን ኮሪያ እንደምትለው የተደረገው የተምዛግዛጊና ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ ህዋሶንግ-12 የሚባለው ነው።

ደቡብ ኮሪያና ጃፓን እንዳመኑት ደግሞ ይህ ተወንጫፊ ሚሳኤል ከጃፓን አቅራቢያ ከሚገኝ የውሃ አካል ከማረፉ በፊት 2ሺ ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ መድረስ ችሎ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ ይፋ ያደረገቻቸው ምስሎች የሚሳኤሉ ፊተኛ ክፍል አረር ላይ በተገጠመ ካሜራ እንደተነሱ ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ለ7ኛ ጊዜ ያደረገችውን ሙከራ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያች በጠንካራ ቃላት አውግዘውታል፡፡

ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ይህ ሚሳኤል 800 ኪሎ ሜትር ተወንጭፎ ለመድረስ የወሰደበት ጊዜ 30 ደቂቃ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ሰሜን ኮሪያ ከኑክሊየርም ይሁን ከማንኛውም ተወንጫፊ የሚሳኤል ሙከራዎች አግዷታል፡፡

ሆኖም የምሥራቅ እስያዋ አገር ሰሜን ኮሪያ ይህን እግድ ቸል በማለት ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጉን ገፍታበታለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ የፈረንጀቹ አዲስ ዓመት በገባ በዚህ በጥር ወር ብቻ ሰባት የተወንጫፊ ሚሳኤል ተኩስ ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡

የአካባቢውን ፖለቲካ ለሚታዘቡ ተንታኞች ይህ ተደጋጋሚ ሙከራ ዋነኛ ግቡ ኪም ጆንግ ኡን የአሜሪካ አቻቸውን ጆ ባይደንን ወደ ድርድር እንዲመጡ ለማስገደድ ያለመ ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባላንጣ አድርጋ የምትመለከታት ደቡብ ኮሪያ በቅርብ ጊዜ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውስጥ ለመግባት ዝግጅት እያደረገች ስለሆነ ለመጪው መሪ ጠንካራ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ተብሏል፡፡