ማይክል ኬ ዊሊያምስ፡ ለአሜሪካዊው ተዋናይ ሞት ምክንያት የሆነውን አደንጻዥ እጽ ሸጠዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

ማይክል ኬ ዊሊያምስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካዊው ተዋናይ ማይክል ኬ ዊሊያምስ ከመሞቱ በፊት ከመጠን በላይ የወሰደውን አደንዛዥ እጽ ሸጠውላታል የተባሉ አራት ግለሰቦች በኒው ዮርክ እና በፖርቶ ሪኮ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በኤች.ቢ.ኦ. ቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም የሆነው 'ዘ ዋየር' ላይ ኦማር የሚለውን ገጸ ባህርይ ወክሎ በመጫወት ዝናን ያተረፈው ዊሊያምስ በብሩክሊ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሞቶ የተገኘው መስከረም 2021 ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦችም በአደንዛዥ እጽ ሴራ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ፖሊስ እንዳለው ግለሰቦቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ የአደንዛዥ እጽ ሞት ምክንያት ነው የተባለውን ፌንታኒል የተባለ በቤተ ሙከራ የተቀመመ አደንዛዥ እጽ ሸጠውለታል።

ፌንታኒል ሰዎች ለህመም ማስታገሻ እና ለመዝናኛ የሚጠቀሙበት አደንዛዥ እጽ ሲሆን ከመጠን በላይ ከተወሰደ ለሞት የሚዳርግ ነው።

የህክምና መርማሪም የ54 ዓመቱ ተዋናይ ሕይወቱ ያለፈው በአደጋ ነው ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ሄክቶር ሮብልስ፣ ሊዩስ ክሩዝ እና ካርሎስ ማሲ ማክሰኞ እለት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ረቡዕ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አርቪን ካርታጀናም ማክሰኞ እለት በፖርቶ ሪኮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ሐሙስ ዳኛ ፊት ይቀርባል ተብሏል።

የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ደሚያን ዊሊያምስ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባሳወቁበት መግለጫ ላይ " ይህ የኅብረተሰብ ጤና ቀውስ ነው፤ መቆም አለበት" ብለዋል።

"ገዳይ የሆኑት እንደ ፌንታኒል እና ሄሮይን ያሉ ኦፒዮድስ አደገኛ ንጥረ ነገርን የያዙ እጾች ማንንም አይመርጡም። ሱስ ውስጥ በመክተት ሕይወትን ወደ አሳዛኝ ሁኔታ ይለውጣሉ" ብለዋል አቃቤ ሕጉ።

መርማሪዎች ዊሊያምስ ሞቶ ከመገኘቱ ከአንድ ቀን በፊት መንገድ ላይ አደንዛዥ እጹን ለዊሊያምስ ሸጠዋል የተባሉትን ግለሰቦች የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከደኅንነት ካሜራ አግኝተዋል።

እጹን ለዊሊያምስ ሸጠዋል የተባሉትን ግለሰቦች የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, DOJ

ግለሰቦቹ አደንዛዥ እጾቹ ዊሊየምስን እንደገደሉት ካወቁ በኋላም በማንሃታን እና ብሩክሊን በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች መሸጥ መቀጠላቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

እንደ ዴይሊ ቢስት የዜና ድረ ገጽ ከሆነ የኒው ዮርክ ፖሊስ መሥሪያ ቤት የተዋናዩን ሞት መንስኤ የተመለከተው እንደ ግድያ በመሆኑ የተጠርጣሪዎቹን የተሽከርካሪ ታርጋ ቁጥር ለመፈለግ በመላ ከተማዋ የደኅንነት ካሜራዎችን ተጠቅሟል።

አንድ የፖሊስ ባለሥልጣን ለፖሊስ መኮንኑ "ይህንን ጉዳይ ማይክል ኬ ዊሊያምስ በጥይት እንደተመታ አድርገህ ያዘው" ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል። በኋላ ላይም ለዜና ድረ ገጹ " በጥይት እንደተመታ እመኑ" ብሏል።

ዊሊያምስ ስመ ጥር በሆነው የኤሚ ሽልማት ሦስት ጊዜ በእጩነት የቀረበ ሲሆን ባለፉት ዓመታት ከአደንዛዥ እጾች ጋር ስለነበረው ትግል በግልፅ ሲናገርም ነበር።

ከፍተኛ አድናቆትን ባተረፈው 'ዘ ዋየር' ተከታታይ ፊልም ኦማር ሊት የተባለ፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ፣ የጎዳና ላይም የእፅ አዘዋዋሪ ዋነኛ ሰውን የወከለ ገፀ ባህርይ ተጫውቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2010 'ብሮድ ዋክ ኢምፓየር' በሚለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም አልበርት 'ቻኪ' ዋይት የተባለ ኃይለኛ ወንበዴን ወክሎ ተጫውቷል።

በአውሮፓውያኑ 1966 በኒውዮርክ ውስጥ የተወለደው ዊሊያምስ ወደ ትወና ሙያው ከመግባቱ በፊት ዳንሰኛ ሆኖ ከሙዚቀኞቹ ማዶና እና ጆርጅ ሚካኤል ጋር ሰርቷል።

ከዚያም በተጨማሪ ስመ ጥር በሆኑ ናሺናል ብላክ ቲያትር ኩባንያም አገልግሏል።