የመንግሥታቱ ድርጅት በየመን እስር ቤት ላይ የደረሰውን የአየር ጥቃት አወገዘ

በአየር ጥቃቱ የወደመው እስር ቤት ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Ansarullah Media Center

የምስሉ መግለጫ, በአየር ጥቃቱ የወደመው እስር ቤት ክፍል
ታትሟል

በሰሜን ምዕራብ የመን የሁቲ አማጺያን ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ሰአዳ በሚገኝ እስር ቤት ላይ ትላንት አርብ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ከ70 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሲሆን ጥቃቱን የመንግሥታቱ ድርጅት አውግዞታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ "እየተካረረ የመጣው ጦርነት መቆም አለበት" ብለዋል። የሁቲ አማጺያንን የሚዋጋው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር ዛሬ ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ የአየር ጥቃቱን አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል።

ጥምረቱ በተጨማሪም ቦታው ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ስምምነት ተደርጎባቸው ለጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ ከተቀመጡ ዝርዝሮች ውጪ ነው ያለ ሲሆን፤ በቀይ መስቀልም ሪፖርት አልተደረገም ብሏል። ሁለቱ ኃይሎች ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲዋጉ ቆይተዋል።

በጦርነቱ ቀጥተኛ ውጤትም 10 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ህጻናትን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ተገድለዋል፣ እንዲሁም አካላቸውን አጥተዋል። ጦርነቱ ሚሊዮኖችን ከቀዬያቸው ሲያፈናቅል አብዛኛው የየመን ሕዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛል።

አርብ ከተፈጸመው የአየር ጥቃት በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች አሁንም አስክሬኖችን ከፍርስራሾች ስር ውስጥ እያወጡ ሲሆን በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ እየደበዘዘ መምጣቱን የቢቢሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ዘጋቢ አና ፎስተር ተናግራለች። ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ድንበር የለሽ ሐኪሞች (ኤምኤስኤፍ) ቢያንስ 70 ሰዎች መሞታቸውን ሲገልጽ ቁጥሩ ግን ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል።

በሁቲ አማጺያን የሚተዳደረው ቴሌቭዥን ሰዎች በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ፍርስራሾችን በእጃቸው ሲያጸዱ እና የቆሰሉ ሰዎችን ሲያነሱ የሚያሳዩ ምስሎችን አስተላልፏል።

ድንበር የለሽ ሐኪሞች እንዳለው አንድ ሆስፒታል ከ200 በላይ ተጎጂዎችን ተቀብሏል።

"የአየር ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ አሁንም ብዙ አስክሬኖች ይገኛሉ፤ በርካታ የጠፉ ሰዎች አሉ። በርግጠኝነት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ማወቅ አይቻልም። ይህ አሰቃቂ የኃይል እርምጃ ይመስላል" ሲሉ የየመን የኤምኤስኤፍ ኃላፊ አሕመድ ማሐት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ስር በደቡባዊ የመን በምትገኘው ሁዳይዳህ የወደብ ከተማ በቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሦስት ሕጻናት እግር ኳስ ሲጫወቱ መሞታቸውን የሕጻናት አድን ድርጅቱ ሴቭ ዘ ቺልድረን አስታውቋል።

በተመሳሳይ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ሊባል የሚችለረ የኢንተርኔት መቋረጥ ተከስቷል።

የሁቲ የመገናኛ ብዙኃን በቴሌኮሙኒኬሽን ጣቢያው ላይ የተፈጸመው ጥቃት በዚህ ምክንያት መሆኑን ጠቅሶ ጥምር ጦሩን ተጠያቂ አድርጓል።

የሳውዲ አረቢያ መንግሥት እንዳለው ጥምር ጦሩ በሁዳይዳ የአየር ጥቃት ፈጽሟል። የሁቲ አማጺያን ባለፈው ሰኞ እለት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤል ጥቃት ካደረሱ በኋላ ጥምረቱ የአየር ድብደባውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በኤምሬትስ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ በተባለው በዚህ ጥቃት ሦስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።