አሜሪካ በረራ ያስቀየሩ አራት የቤላሩስ ባለሥልጣናትን 'በውንብድና' ከሰሰች

ታትሟል

ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ግንቦት አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን በግድ ሚንስክ እንዲያርፍ ያደረጉ አራት የቤላሩስ ባለሥልጣናትን በውንብድና ከሳለች።

የሕግ አዋቂዎች እንደሚሉት ባለሥልጣናቱ የቦንብ አደጋ እንዳለ በማስመሰል ተቃዋሚው ፖለቲከኛና ጋዜጠኛ ሮማን ፕሮታሴቪሽ ተሳፍሮበት የነበረውን አውሮፕላን ቤላሩስ አሳርፈዋል።

ራያንኤይር በተሰኘው አየር መንገድ በኩል እየበረሩ የነበሩት ባለሥልጣናት በአየር በረራ ውንብድና ነው የተከሰሱት።

ወንጀል መርማሪው ኤፍቢአይ እንዳለው ድርጊቱ "በቸልተኝነት የተፈፀመ የሕግ ጥሰት ነው"።

በዚህ ወር መባቻ የተባበሩት መንግሥታት የቦንብ አደጋ ነበር ተብሎ የተነገረው ሃሰት ነው ብሎ ነበር።

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ሌዮኒድ ሚካሌቪች፣ ኦሌግ ካዙቺትስ፣ አንድሬ አናቶሊዬቪች እና ፍኑ ልኑ የተባሉት አራቱ ባለሥልጣናት አሁን ቤላሩስ ውስጥ ይገኛሉ።

አሜሪካ ውስጥ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ይጠብቃቸዋል።

ክሱ እንደሚያመለክተው ቹኖ የተባሉት ግለሰብ የቦንብ ጥቃት ሊደርስ ይችላል በማለት አውሮፕላኑ ከግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ወደ ሊቱዌኒያ ከመብረሩ በፊት ለቤላሩስ አየር መቆጣጠሪያ ሰዎች ተናግረዋል።

የአየር መቆጣጠሪያ ባለሥልጣናቱ አውሮፕላኑ የቤላሩስ አየር ክልል እስኪገባ ድረስ ጠብቀው ለአብራሪው የቦንብ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ሚንስክ እንዲያርፍ ነግረውታል።

የቹኖ ምክትል የሆኑት ካዙቺትስ በበኩላቸው ሃሰተኛ የቦንብ ጥቃት አለ ተብሎ አውሮፕላኑ እንዲያርፍ መደረጉንና ባለሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን ደብቀዋል ተብለው ተከሰዋል።

ክሱ ኒው ዮርክ ውስጥ ባለ አንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት ከተመሠረተ በኋላ የኤፍቢአይ ምክትል ዳይሬክተር ማይክል ድሪስኮል አውሮፕላን ጠለፋውን "በግድየለሽነት የአሜሪካን ሕግ መጣስ ነው" ሲሉ ገልፀውታል።

"በቀጣይ አንድ አውሮፕላን አብራሪ መሰል መልዕክት ቢደርሰው የመልዕክቱን እውነተኛነት ሊጠራጠር ይችላል። ይህ ደግሞ የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የራያንኤይር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማይክል ኦሊሪ ክስተቱን "መንግሥት ያቀነባበረው የአውሮፕላን ጠለፋ" ብለውት ነበር።

አውሮፕላኑ በግዴታ ቤላሩስ እንዲያርፍ በተደረገ ወቅት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና ዩናይትድ ኪንግደም ቤላሩስ ላይ ማዕቀብ ጥለው ነበር።

በወቅቱ የቤላሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቦንብ አደጋው ሊከሰት የሚችል እንደነበር ጠቅሰው ይህንን ያደረጉት "ለሃገራቸውን ደኅንነት በማሰብ እንደሆነ" ተናግረው ነበር።

ኔክስታ የተባለው የተቃዋሚ አውታር ጋዜጠኛ የሆነው የ26 ዓመቱ ሮማን ፕሮታሴቪሽ እና የፍቅር አጋሩ ሶፊያ ሳፔጋ ሚንስክ እንዳረፉ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ፕሮታሴቪሽ ባለፈው ሰኔ ከእስር ተለቆ ያለፉትን ሰባት ወራት በቁም እስራት ላይ ይገኛል።

ቤተሰቦቹ ባለፈው ኅዳር ለቤላሩስ መገናኛ ብዙሃን ድምፃቸውን በሰጡበት ወቅት ያለማቋረጥ እንዲጎበኙት እንደተፈቀደላቸው ተናግረው ነበር።

ቤላሩስን በፈረንጆቹ ከ1994 ጀምሮ የመሩት ሉካሼንኮ በ2020 የተደረገውን ምርጫ በሰፊ ድምፅ አሸንፊያለሁ ማለታቸው ከባድ ተቃውሞ እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ በኋላ ፕሬዝደንቱ ተቃውሞ የሚያነሱና የሚቀሰቅሱ ሰዎች ላይ ከባድ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።