ሩስያ እና አሜሪካ ከተወያዩ በኋላ የዩክሬን ስጋት መቃለሉ ተሰማ

ታትሟል

ሁለቱ ሃያላን ሀገራት ባለስልጣናት በጄኔቫ በከፍተኛ ደረጃ ውይይት ለማድረግ ከተገናኙ በኋላ ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ሀሳብ እንደሌላት ለአሜሪካ ተናግራለች።

ትላንት ሰኞ ሰባት ሰአታት ከፈጀው ምክክር በኋላ በአከባቢው ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀጠል ሁለቱም ሀገራት ተስማምተዋል።

ሆኖም ከዚህ ውይይት በኋላ የተደረገ መሰረታዊ ለውጥ ስለመኖሩ ምንም የታየ ምልክት የለም።

ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን ጋር በሚያዋስኑት ድንበር አቅራቢያ እንደሚገኙ ይታመናል። ይህም ዩክሬን በሩስያ ልትወረር ትችላለች በሚል ምዕራባውያን ማስጠንቀቂያ አስከትሏል።

አሜሪካ ሩሲያ ዩክሬንን የምታጠቃ ከሆነ ማዕቀብ እንደሚኖር ስትገልጽ ቆይታለች።

ሩሲያ በበኩሏ ሞስኮ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምታደርገውን ግጭት አሜሪካ ከተሳተፈች "አደጋውን አሳንሳ እንዳትመለከት" አስጠንቅቃ ነበር።

የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ ከስብሰባው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ዩክሬንን ለማጥቃት ምንም እቅድ እና አላማ እንደሌለን ለባልደረባዎቻችን አስረድተናል" ብለዋል።

ሩሲያውያኑ ባለስልጣናት ለአሜሪካ አቻዎቻቸው "ሀገራቸው የውጊያ ስልጠና የምታደርገው በግዛቷ ውስጥ ነው" ያሉ ሲሆን "ከዚህ አኳያ ድንገተኛ ሁኔታን ይፈጠራል በሚል የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ" ተናግረዋል ።

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሸርማን ምክክሩ የሁሉም ወገን የጸጥታ ስጋት ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንደኖር ለማበረታታት የደረገና "ግልጽ እና ቀጥተኛ " ውይይት ነው ብለዋል።

የሩሲያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በዩክሬን ጉዳይ ፊት ለፊት ለመወያየት ሲቀመጡ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ኔቶ ከምስራቅ አውሮፓ እንዲወጣ ሩሲያ በአካል ጥያቄ ያቀረበችበት ነው።

ይህ ውይይት አበረታች ነው ቢባልም በሀገራቱ መካከል ያለው ክፍተት ሰፊ ነው። አሜሪካ ሩሲያ ውጥረቱ እንዲረግብ እና ወታደሮቿን ከዩክሬን ድንበር እንድታነሳ በውይይት አሳሰበች ነገር ግን ይህ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ አላገኘችም።