ፓኪስታን ውስጥ በከባድ የበረዶ ወጀብ ምክንያት ቢያንስ 21 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሰሜናዊ ፓኪስታን መኪናቸው ውስጥ ሳሉ በከባድ በረዶ መውጫ ያጡ ቢያንስ 21 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተዘገበ።
አሁንም የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በኮረብታ ጫፍ ላይ ባለችው ሙሬ ከተማ አቅራቢያ በከባድ በረዶ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሰዎች መንቀሳቀሻ እንዲያገኙ ለማስቻል በመንገዶች ላይ ያለውን የበረዶ ክምር ለማጽዳት እየሞከረ ነው።
የአገሪቱ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሼክ ራሺድ እንደተናገሩት በዋና ጎዳና ላይ በጣለው ከባድ በረዶ ምክንያት 1,000 የሚደርሱ መኪኖች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ሆነው በበረዶ ተይዘዋል።
ከፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ በስተሰሜን የምትገኘው ሙሬ ተራራማ የመዝናኛ ከተማ ናት። የፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በጣለው ካባድ የበረዶ ወጀብ ምክንያት ቱሪስቶች ከአርብ ዕለት ጀምሮ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ባሉበት እየተጉላሉ ነው።
በቅርብ ቀናት ውስጥ በሙሬ ከተማ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ እየጣለ ያለውን በረዶ ለማየት ከ100 ሺህ በላይ መኪኖች ወደ ከተማዋ ገብተዋል። በዚህም ምክንያት በከተማዋ ውስጥና በዙሪያዋ ባሉ መንገዶች ላይ ከባድ የትራፊክ መጨናነቅ መከሰቱን ፖሊስ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጿል።
የፑንጃብ ግዛት አስተዳዳሪ ጽህፈት ቤት ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ በመምከር ከባድ በረዶ የሚጥልበትን አካባቢ "የአደጋ ስፍራ" እንደሆነ አውጇል።
"ከ15 አስከ 20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች ወደ ሙሬ በመጉረፋቸው ከባድ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል" ሲሉ ሚኒስትሩ ራሺድ በቪዲዮ ባስተላለፉት ምልዕክታቸው ላይ ተናግረዋል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን በ ጎብኝዎች ላይ በደረሰው "አሰቃቂ ሞት" የተሰማቸውን ድንጋጤ ገልጸዋል።
"በደረሰው አደጋ ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ እና እንዲህ ያለውን አሰቃቂ አደጋ ለመከላከል ጠንካራ ደንብ ተግባራዊ እንዲሆን አዝዣለሁ" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።












