በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና ምላሽ የሚጠብቁት ቤተሰቦቻቸው

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች ጉዳይ በተለይም ታስረው የሚገኙበት ቦታ ያልታወቁ ሁለት ጋዜጠኞች እንዲሁም ቀሪዎቹ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን ተክትሎ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
የአሐዱ ራድዮ ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁን ቤተሰቦቹም ፖሊስም ለአንድ ወር ያህል አላየነውም ማለታቸው አይዘነጋም።
የተራራ ኔትወርክ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ ከታኅሣሥ 01/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት ያለበት ሳይታወቅ ቆይቷል።
የክብሮም አባት እስካሁን ልጃቸው የት እንዳለ እንዳላወቁ እና ነገ ታኅሳስ 12/2014 ዓ. ም. ፍርድ ቤት ቀጠሮ ስላላቸው ፖሊስ የሚለውን በችሎት ለመስማት እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
የታምራት ነገራ ባለቤት ሰላም በላይ በበኩሏ ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ታኅሳስ 07/2014 ዓ. ም. ገላን የሚገኝ ችሎት መቅረቡን በማግስቱ እሷን ጨምሮ ሦስት የቤተሰብ አባላት በጎበኙት ወቅት ማወቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የገላን ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሄደን ነው ያገኘው። የቀረበበትን ክስ አላወቅንም። ደኅና ነኝ አትጨነቁ ብሎናል። ያለበትን ቦታ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳውቀናል። ነገር ግን ከርቀት በጣም ለአጭር ጊዜ ነው የተነጋገርነው። ከ14 ቀን በኋላ እዚያው ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ነግሮናል" ብላለች ባለቤቱ ሰላም።
በዩቲዩብ ላይ የሚተላለፈው የሮሃ ሚዲያ መስራች የሆችው መዓዛ መሐመድ ባለፈው ሳምንት አርብ በቁጥጥር ስር ከምትገኝበት አዲስ አበባ ፖሊስ ወደ አራዳ ምድብ ችሎት ብትወሰድም፤ አብሯት መርማሪ ፖሊስ ባለመሄዱ ብሎም ዳኛው በችሎት ባለመገኘታቸው ጉዳይዋ ሳይታይ መመለሷን ወንድሟ ዩሱፍ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ምናልባት ዛሬ ሰኞ ታኅሳስ 11/2014 ዓ. ም. ችሎት ከተወሰደች በሚል ባለቤቷ በችሎት እየተጠባበቀ እንደሆነ እና እስካሁን ድረስ ግን ወደ ችሎት አለመወሰዷን ወንድሟ ገልጿል።
መዓዛ ካሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ጉንፋን የሚመስል ሕመም እንደጀመራት እና እስካሁን ድረስ ግን ሕክምና ጠይቃ አለማግኘቷን ዩሱፍ ገልጿል።
"ይቆረጥመኛል ትላለች። በታሰሩበት ቦታ ከ50 ሰው በላይ ሰው እንዳለ እና ማስክን ጨምሮ ምንም አይነት ጥንቃቄ አለመኖሩን ተናግራለች" ሲል ወንድሟ ገልጿል።
"የእሷ መታሰር ሙሉ ቤተሰቧን አስጨንቋል። ከወለጋ ቤተሰቧን ያጣች ልጅ አምጥታ ታሳድጋለች። የራሷ ልጅ እንዳለች ሆኖ፤ አስኮ አካባቢም የምታሳድጋቸው ልጆች አሉ። የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጧት እንፈልጋለን" በማለትም አክሏል።
በተመሳሳይ በተለምዶ ሦስተኛ ተብሎ በሚታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ማቆያ ውስጥ የሚገኘው የእያስፔድ ተስፋዬ እናት ወ/ሮ ተሻለች፤ ልጃቸውን የጠየቁ ወዳጆቹ መታመሙን እንደገለጹላቸው እና እርሳቸው ግን ስለታመሙ እስካሁን ሄደው እንዳላዩት ተናግረዋል።
"ሰው ለምኜ ነው የምልከው። ጥርሱን ስለሚያመው የሚጠቀመው መድኃኒትነት ያለው የጥርስ ሳሙና ነበር። እሱን ላኪልኝ ብሎ ልኳል። እንግዲህ ጥርሱን አሞት ይሆናል ብዬ አሰብኩ። እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረበም። ጠበቃም ልናቆምለት እንፈልጋለን" ሲሉ ወ/ሮ ተሻለች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በተከታታይ ቀናት ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው ስለተወሰዱት ስለእያስፔድ፣ ታምራትና መዓዛ እንዲሁም ከሁለት ወር በፊት በቁጥጥር ስር ስለዋለው ክብሮም አስካሁን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ቢቢሲም ከፖሊስና ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።












