የሜክሲኳዊው እጽ አዘዋዋሪ ኤል ቻፖ ባለቤት የሦስት ዓመታት እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
የታዋቂው ሜክሲኳዊ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ዮአኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን ባለቤት የሆነችው ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ የሦስት ዓመት እስር ተፈረደባት።
ኤማ ይህ ፍርድ የተላለፈባት የባለቤቷን ሲናሎአ ተብሎ የሚጠራ አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ድርጅት በመደገፏ ነው ተብሏል።
የ32 ዓመቷ ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ ሰኔ ወር ላይ ሴራ ከመጠንሰስ እስከ አደንዛዥ እጽ ማዘዋወር ድረስ ክስ ቀርቦባት ጥፋተኛ መሆኗን አምናለች።
በተጨማሪም ኤልቻፖ ጉዝማን ከሜክሲኮ እስር ቤት እንዲያመልጥ እንደረዳችው ኤማ ቃሏን ሰጥታለች።
ኤማ ጥፋተኝነቷን ባመነችበት ክስ የእድሜ ልክ እስራት ሊያስፈርድባት የሚችል ቢሆንም በድርጊቷ መጸጸቷን በመግለጿ የአሜሪካ አቃብያነ ህግ አጭር የእስር ቅጣት እንዲወሰን ጠይቀዋል።
ባለቤቷ ኤልቻፖ በአሁኑ ሰዓት በኮሎራዶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት የቀድሞዋ 'የቁንጅና ንግሥት' ኮሮኔል አይስፑሮ ከጉዝማን ከኤልቻፖ እና ከሌሎች የሲናሎአ ካርቴል የእጽ አዘዋዋሪው ቡድን አባላት ጋር ኮኬይን፣ ሄሮይን፣ ሜታንምፌታሚን እና ማሪዋናን የሚባሉ አደንዛዥ እጽ ወደ አሜሪካ ለማዘዋወር እና የተገኘውን ገንዘብ በሕገ ወጥ መልኩ ለመጠቀም በነበረው ሴራ ተሳታፊ ነበረች።
ባለሥልጣናቱ ኤማ አይስፑሮ እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ኤልቻፖ ታስሮ ከሚገኘበት እስር ቤት አቅራቢያ ያለ ቦታን በመግዛት ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግበት እስር ቤት እንዲያመልጥ "ወሳኝ ሚና" ተጫውታለች ብለው ያምናሉ።
ኤልቻፖ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ውስጥ ለውስጥ በተቆፈሩት ዋሻ ማምለጥ የቻለ ሲሆን ይህ የአየር ማስተላለፊያ ቱቦዎች እና መብራት የተገጠመለት ሲሆን ሞተር ሳይክል መሄድ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነበር።
ይህም የተሟላው በእጽ አዘዋዋሪ ቡድኑ ካርቴል ገንዘብ እንደሆነ ታምኗል።
በዚህ ወንጀልም ባለቤቱ ቦታ ጠቋሚ [ጂፒኤስ] የተገጠመለት የእጅ ሰዓት ያቀረበችለት ሲሆን ኤልቻፖ ውስጥ እያለ ለተልዕኮ መልእክት አስተላልፋለች። በዚህ ሁኔታ የተሰወረው ኤልቻፖ ለቃለ ምልልስ ብቅ እስኪል ድረስ የት እንዳለ አልታወቀም ነበር።
ትላንት ማክሰኞ በዋሽንግተን ፍርድ ቤት በነበረው ችሎት ባለቤቱ የ1.5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዲወረስ እና ከእስር ስትወጣ ለአራት አመታት ክትትል እንዲደረግባት ውሳኔ አሳልፏል።
ኤማ በስፓኒሽ ቋንቋ በአስተርጓሚ ለፍርድ ቤቱ ስታስረዳ "የፈጸምኩት ድርጊት ላስከተለው ማንኛውም ጉዳት እውነተኛ ፀፀት ተሰምቶኛል" ብላለች።
የአሜሪካ የፌደራል አቃቤ ህግ የተከሳሿ ተሳትፎ "የጎላ" ቢሆንም ሚናዋ በጣም አናሳ እንደሆነ በመጠቀስ እና "በወንጀሉ የነበራትን ተሳትፎ ሳታቅማማ ተቀብላለች" ብሏል።
በአሜሪካ የተወለደችው ኤማ የሲናሎአ ካርቴል የእጽ አዘዋዋሪ አባል ከሆነው ኤልቻፖ ጋር በ17 ዓመቷ ተገናኝተው በሚቀጥለው ዓመት በትዳር ተጣመሩ።
አባቷ እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 በሜክሲኮ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው እስር ቤት ይገኛሉ። አጎቷ ኢግናሲዮ ኮሮኔል ቪላሪያል ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ከሜክሲኮ ጦር ጋር በነበራቻው የተኩስ ልውውጥ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ በሜክሲኮ በጣም ከሚፈለጉ ወንጀለኞች አንዱ ነበሩ።












