በወሲባዊ ጥቃት የተከሰሰው አሜሪካዊው ተዋናይ 31 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፍል ነው

ኬቪን ስፔሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

'ሃውስ ኦፍ ካርድስ' በተሰኘው ተከታታይ ፊልም መሪ ተዋናይ የነበረው ኬቨን ስፔሲ በፊልሙ ቀረጻ ወቅት አድርሶታል ለተባለው ወሲባዊጥቃት ፊልሙን ላሰራው ሰቱዲዮ 31 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል በመሃላቸው ያለው አደራዳሪ መወሰኑ ታወቀ።

ውሳኔው በሚስጥር ከ አንድ አመት በፊት የተሰጠ ሲሆን ኤምአርሲ የተሰኘው ስቱዲዮው ሰኞ ዕለት ካሳው እንዲከፈለው ማረጋገጫ ለመጠየቅ ወደ ፍርድ ቤት ካመራ በኋላ ነው ይፋ የወጣው።

ተዋናዩ ባለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ የወሲባዊ ጥቃት ክሶች የመጡበት ሲሆን ስፔሲ ግን ምንም አይነት ጥፋት አልፈጸምኩም ሲል ተከራክሯል።

የቀረቡበትን የጥቃት ክሶች ተክትሎ የ62 ዓመቱ ስፔሲ በሃውስ ኦፍ ካርድስ ፊልም ላይ ያለውን ሚና የተነጠቀ ሲሆን ''መርዛማ'' የስራ ቦታ ከባቢ በመፍጠር፣ ክፋት የተሞላባቸው አስተያየቶችን በመስጠት ብሎም ወጣት ሰራተኞችን ያለፈቃዳቸው አካላቸውን በመንካት ክስ ቀርቦበታል። እነዚህ ክሶች ከቀረቡበት ወዲህም ስፔሲ ከአይን ርቆ ቆይቷል።

በሆሊውድ ውስጥ በይፋ አግባብ ያልሆነ ተግባራትን በመፈጸም ክስ ከቀረበባቸው ጥቂት ተዋናዮች መካከል ስፔሲ አንዱ ሲሆን በተመሳሳይም ሃርቬይ ዊንስተን ላይ የቀረበቡት ክሶች ይታወሳሉ።

የሃርቬይ ክስን ተከትሎ 'ሚቱ' የተሰኘ ከፍተኛ የጸረ ጸታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ መነሳቱ ይታወሳል። ሃርቬይ የቀረበበትን ክሶች ተከትሎ ኔት ፍሌክስም ሆነ ፊልሙን የሚሰራው ስቱዲዮ ከፊልሙ ስክሪፕት ላይ ያለው የመሪ ተዋናይነት በሌላ እንዲተካ ድርሰቱ እንዲቀየር አድርገዋል።

ይህንን ተከትሎም ስቱዲዮው በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ማጣቱን የድርድር ወረቀቱ ያሳያል። እንዲሁም ከሁለቱም ወገን የተመረጡ የሕግ ባለሞያዎች የ20 ሰዎችን ቃል በስምንት ቀናት ውስጥ ሰምተዋል።

ስፔሲ እንዲከፍል የተወሰነበት ገንዘብ የካሳ ክፍያ፣ የጠበቃ ክፍያ እና የችሎት ወጪዎችን ጨምሮ ነው 31 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል የተወሰነበት።

በውሳኔው ላይ ይግባኝ ቢጠይቅም በያዝነው ወር ይግባኙ ውድቅ ተደርጎበታል። የመጀመሪያው ክስም አንቶኒ ራፕ ከተሰኘው የፊልም ተዋናይ የቀረበ ሲሆን በ 14 ዓመቱ ወሲባዊ አቀራረብ ያላቸው ተግባራት ተፈጽመውብኛል ሲል ነበር ክሱን ያቀረበው።

ስፔሲ ተግባሩን እንደማያስታውስ እና ለ ራፐሩ ግን ጥልቅ የሆነ ይቅርታ እንደሚጠይቅ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር።

በዚሁ መግለጫ ላይ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆኑንም ይፋ ያደረገ ሲሆን የወሲባዊ ጥቃትን ከተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አፍቃሪነቱ ጋር በማያያዙ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል።

ከዚህ በመቀጠልም በርካታ ተመሳሳይ ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በካሊፎርኒያ ያለ ማሳጅ ቤት ሰራተኛ ተመሳሳይ ክስ ቢያቀርብም ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሳይደርስ ህይይወቱ አልፏል።

እነዚህን ክሶች ተከትሎም ስፔሲ በርካታ የትወና ስራዎችን ያጣ ሲሆን በመጨረሻም ግን በትንሽ ገንዘብ የሚሰራ ፊልም ላይ አነስተኛ ድርሻ ተሰጥቶት ወደ ትወናው ተመልሷል።