የአማዞን ህንድ የስራ አስፈፃሚዎች በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክስ ተመሰረተባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በህንድ የአማዞን ኩባንያ ተቀጥረው የሚሰሩ ሁለት ሰራተኞች የኩባንያውን የመገበያያ ድረ-ገጽ በመጠቀም አደንዛዥ ዕፅ (ዕፀ ፋርስ) ሲያዘዋውውሩ መገኘታቸውን ተከትሎ የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ባለፈው ሳምንት በፕራዴሽ ግዛት ፖሊስ 20 ኪሎ ግራም ማሪዋና ወደ ሌሎች የህንድ ግዛቶች ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ፖሊስ እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ አደንዛዥ ዕፁን የተፈጥሮ ጣፋጭ በማስመሰል በኩባንያው ድረገፅ ላይ ማሪዋና ይገበያዩ ነበር።
አማዞን ለህግ አስከባሪ አካላት መረጃ እያጋራ መሆኑን ተናግሯል።
"አማዞን ለሥነ ምግባር ጉድለት ምንም አይነት ቦታ የለውም።ፖሊሲያችንን ወይም አግባብነት ያላቸውን ህጎች በመጣስ ግለሰቦች ወይም ሶስተኛ ወገኖች ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወስዳል" ብሏል ኩባንያው።
ኩባንያዎቹ ህገ-ወጥ ምርቶችን መዘርዘርና መሸጥ እንደማይፈቅድ ገልፆ ህገ-ወጥ እቃዎች ላይ ያወጣውን ህግ ጥሰው በተገኙ ሻጮች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
የግዛቱ ፖሊስ የአማዞን ህንድ ዋና ዳይሬክተሮች በናርኮቲክ መድኃኒቶች እና ሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ህግ መሰረት ክስ እንደተመሰረተባቸው ተናግሯል።
የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ክስ የተመሰረተባቸው ምክንያት ፖሊስ ሲያስረዳ " ኩባንያው ለፖሊስ ጥያቄዎች በሰነድ የመለሰውና በውይይት ወቅት የተሰጡ ምላሾች ልዩነት ነው" ብሏል።
ባለስልጣናቱ ምን ያህል ስራ አስፈፃሚዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው አልገለፁም።
በዚህ ዝውውርም ወደ 148 ሺህ ዶላር የሚያወጣ 1 ሺህ ኪሎግራም ማሪዋና ድረ-ገጹን ተጠቅሞ ለሽያጭ ቀርቧል የሚል ግምት እንዳለም ተጠቅሷል።
የአሜሪካ ዙፍ የችርቻሮ ንግድ ድርጅት ዋልማርት ቅርንጫፍ ከሆነው ፍሊፕካርት ጋር፣ አማዞን ህንድም ለአንዳንድ ሻጮች አዳልተዋል በሚል በተቆጣጣሪዎች ፍተሻ እየተደረገበት ይገኛል።
በያዝነው ዓመት ላይ አማዞን አንድ ወይም ከዚያ በላይ የህንድ ሰራተኞቹ ለባለስልጣናት ጉቦ ሰጥተዋል መባሉን ተከትሎ ኩባንያው የውስጥ ምርመራ መጀመሩ ተዘግቧል።












