የአማዞን ደን ባለፉት 15 ዓመታት ያልታየ የደን ጭፍጨፋ ገጥሞታል

የፎቶው ባለመብት, EPA
በብራዚል በሚገኘው የአማዞን ደን ባለፉት 15 ዓመታት ከታዩት እጅግ በባሰ መልኩ የደን ጭፍጨፋ እየተካሄደ መሆኑን እንድ ይፋዊ ጥናት አመለከተ።
የብራዚል የሕዋ ሳይንስ ምርምር ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በጫካው ውስጥ የተስተዋለው የደን ምንጣሮ 22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ግላስኮው በተካሄደው ኮፕ26 የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ በአውሮፓውያኑ 2030 የደን ጭፍጨፋን ለማጥፋት እንሠራለን ካሉት በርካታ አገራት መካከል ብራዚል አንደኛዋ ነች።
የአማዞን ጥቅጥቅ ደን እጅግ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ሲሆን በውስጡም እስከ ሦስት ሚሊየን የሚደርሱ የተክልና የእንስሳት ዝርያዎችን ይዟል። በተጨማሪም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ቀደምት ነዋሪዎች ይገኙበታል።
ይህ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነው ደን በከፍተኛ ሁኔታ ካርቦን የመሰብሰብ አቅም ያለው ሲሆን የዓለማችንን ሙቀት ከሚቆጣጠሩት ተፈጥሯዊ አካላት አንዱ ነው።
የብራዚል የሕዋ ሳይንስ ምርምር ኤጀንሲ የሰበሰበው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ 13 ሺህ 235 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሬት በአውሮፓውያኑ ከ2020 እስከ 21 ጊዜ ውስጥ ብቻ ተመንጥሯል። ይህ ደግሞ በ2006 ከታየው ከፍተኛ የደን ምንጣሮ በላይ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የአገሪቱ የከባቢ አየር ሚኒስትር የሆኑት ጆአኪም ሌይት እንዳሉት፤ የተገኘው መረጃ ችግሩ ምን ያህል አስከፊ እንደሆን ማሳያ ነው። አክለውም ሚኒስትሩ ''መሰል ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ሰዎች ለመያዝና ለመቆጣጠር ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል'' ሲሉ ተደምጠዋል።
በአስደናዊቂው የአማዞን ደን ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ በአሁኑ ፕሬዝዳንት ጃዬር ቦልሶናሪ አስተዳደር ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይገለጻል። ፕሬዝዳንቱ በጫካው አካባቢ ግብርና እንዲሁም የማዕድን ማውጣት ሥራዎች እንዲከናወኑ ያበረታታሉ።
ፕሬዝዳንቱ የብራዚል የሕዋ ሳይንስ ምርምር ኤጀንሲ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች የሚተቹ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2019 ኤጀንሲው ያወጣውን ሪፖርት የአገርን ምስል የሚያጎድፍ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን በያዝነው ሳምንት በተጠናቀቀው ኮፕ26 የአየር ንብረት ስብሰባ ላይ የደን ምንጣሮ እና የከሰል አጠቃቀም ላይ አገራት ከስምምነት ሲደርሱ ብራዚልም ደግፋለች። የጋራ ስምምነቱንም ፈርማለች።
በስምምነቱ መሠረት አገራቱ እስከ 19.2 ቢሊየን ዶላር ድረስ አሰባስበው ገንዘቡ በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ለሚሠሩ መሬትን መልሶ የማገገም ሥራዎች፣ የዱር ሰደደን መቆጣጠር እና የአካባቢው ነዋሪዎችን ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።












