ባለቤቱ በኢራን የታሰረችበት እንግሊዛዊ ከ21 ቀናት በኋላ የረሃብ አድማውን አቆመ

ታትሟል

የብሪታኒያ-ኢራናዊ ጥምር ዜግነት ያላትና በኢራን እስር ቤት ውስጥ ያለችው ናዛኒን ዛጋሪ ራትክሊፍ ባለቤት ተቃውሞውን ለመግለፅ ለ21 ቀናት ያደረገው የረሃብ አድማውን አቆመ።

ሪቻርድ ራትክሊፍ ባለቤቱን ለማስለቀቅ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የበለጠ እንዲሰራ ለመጠየቅ ከውጪ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ውጭ ተቃውሞውን በረሃብ አድማ ሲያደርግ ቆይቷል።

ለረሃብ አድማው ለማቆምም ምክንያት የሆነው ለባለቤቱ የገባው ቃል እንደሆነና ልጃቸው "ሁለት ወላጆች ያስፈልጋቸዋል" በማለትም በአሁኑ ወቅት ሙሉ ምርመራ ለማድረግም ወደ ሆስፒታል እንደሚሄድ ተናግሯል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በኢራን ውስጥ በእስር ላይ ያሉ ብሪታንያውያን ለማስለቀቅ የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ናዛኒን ዛጋሪ ራትክሊፍ በኢራን በስለላ ክስ ለአምስት አመት ታስራ የምትገኝ ሲሆን በባለፈው ወር ጥቅምት ሁለተኛ የእስር ቅጣት ላይ ያቀረበችው ይግባኝ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ናዛኒን በአውሮፓውያኑ 2016 ልጃቸውን ጋብሪየላ ጋር በመሆን በኢራን የሚገኙ ቤተሰቦቿን ለመጠየቅ በመጣችበት ወቅት ነበር መንግሥትን ለመገልበጥ በማሴር የተከሰሰችው።

በቴህራን ኤቪን እስር ቤት ለአራት አመታት ያህል የቆየች ሲሆን አንዱን አመት ደግሞ በቁም እስረኝነት ቆይታለች።

ባለቤቷ ሪቻርድ ግላስጎው በተደረገው ኮፕ 25 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኢራን ልዑካንን እንዲያገኙ እና በኢራን ውስጥ ለታሰሩ ብሪታንያውያን ነፃነት እንዲጠይቁ ጫና ለማድረግ ተስፋውን ሰንቆም ነው ከጥቅምት 14፣ 20121 ዓ.ም የተቃውሞ ድምፁን ማሰማት ጀመረ።

ላለፉት ሶስት ሳምንታትም ትንሽዬ ድንኳን ዘርግቶ በሷም ውስጥ እያደረ ምግብ ሳይወስድ በፈሳሽ ነው የቆየው።

ሪቻርድ እንደሚናገረው በአንድ ጀንበር በእግሮቹ መገጣጠሚያ ላይ ህመም እንደጀመረውና ከሐኪሙ ጋር ከተነጋገረ በኋላ የረሃብ አድማውን ለማቆም ውሳኔ ላይ መድረሱን ተናግሯል።

ለባለቤቱ የረሃብ አድማ ተቃውሞው "በአምቡላንስ የሚያስወጣው" ደረጃ ላይ ከደረሰ እንደሚያቆመውና "ደረቱን ነፍቶ ጭንቅላቱን ቀና አድርጎ ከተቃውሞው መውጣት እንደሚፈልግ" መንገሩንም ሪቻርድ ያስረዳል።

ሆስፒታል ከሄደ በኋላም ምግብ ለመመገብ ተስፋ ማድረጉንም ገልጿል።

የረሃብ አድማውን በማቆሙም ሴት ልጁ እፎይታ እንዳገኘችና ቤት በመመምጣቱም ደስተኛ መሆኗን ተናግሮ ከዚህ በኋላም ማገገም እና ቀጣይ እርምጃዎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መወጠን መሆኑንም አስታውቋል።

ባደረገውም ተቃውሞ የባለቤቱ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት እንዳገኘ ተሰምቶኛል ብሏል።

በረሃብ አድማው ወቅት የጎበችው የአካባቢው የፓርላማ አባል ቱሊክ ሲዲቅ በመጪው ማክሰኞ በናዛኒን ጉዳይ ለመምከር ፓርላማው ቀጠሮ እንደያዘና የተለያዩ ፓርቲዎችም ድጋፍ እንዳገኘ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባሏ ከባለቤቱ ናዛኒን ጋር መነጋገራቸውንና የሪቻርድ ሁኔታም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስጨነቃትና ህክምና እንዲያገኝ መጠየቋን ተናግረዋል።

ቅዳሜ አመሻሹም ላይ ሪቻርድ መብላቱንና በጥሩ ጤንነትም ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በረሃብ አድማው ወቅት አልጎበኙም በማለት የተቻቸው ሲሆን ለዓመታት የናዛኒን ጉዳይ በበቂ ሁኔታ አላስተናገዱም እንዲሁም "የገቡትም ቃል አላከበሩም" ሲልተ ተችቷቸዋል።