190 ሃገራት እና ድርጅቶች ከሰል ላለመጠቀም ቃል ገቡ

የከሰል ማምረቻ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊን ጨምሮ ዋና ዋና የከሰል ተጠቃሚዎች በኮፕ26 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እንደ ከሰል፣ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ የኃይል ምንጮችን ላለመጠቀም ቃል ገብተዋል ሲል የእንግሊዝ መንግሥት አስታወቀ።

ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቁ አስተዋፅኦ ካላቸው መካከል ከሰል ቀዳሚው ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እንዳለችው ከሆነ 190 ሃገራት እና ድርጅቶች ከሰል ለማቆም ቃል ገብተዋል ።

እንደ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና አሜሪካ ያሉ አንዳንድ በከሰል ላይ ጥገኛ የሆኑ ቀዳሚ ሃገራት ቃል ከመግባት ተቆጥበዋል።

የስምምነቱ ፈራሚዎች በሃገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የከሰል ኃይልን ከመጠቀም ለማቆም ቆርጠዋል።

እንደ እንግሊዝ ከሆነ በ2030ዎቹ የከሰል ሃይልን ለዋና ኢኮኖሚ እንዲሁም በ2040ዎቹ ደግሞ ለድሃ ሀገራት ከመጠቀም ለማቆም ተስማምተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የንግድ እና ኢነርጂ ፀሐፊ ክዋሲ ክዋርቴንግ "የከሰል ማክተሚያ በቅርቡ እንደሚሆን እየታየ ነው" ብለዋል።

"ዓለማችን በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄደች ነው። የከሰል ዕጣ ፈንታን ለመዝጋት እና ለወደፊቱ በታዳሽ ሃይል የሚንቀሳቀስ የአካባቢ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለመቀበል ዝግጁ ነው።" ብለዋል።

ስምምነቱን ከ40 በላይ ሃገራት ፈርመዋል። ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ከሰል ኃይል ላለመገንባት እና በዘርፉ መዋለ ንዋይ ላለማፍሰስ ከተስማሙ 18 ሃገራት መካከል መሆናቸውን እንግሊዝ ገልጻለች።

የዩናይትድ ኪንግደም ሻዶው (ስልጣን የሌለውን እና መንግስትን ለመከታተል የተቋቋመ ነው) የንግድ ጸሐፊ ኤድ ሚሊባንድ እንደ ቻይና ያሉና ሌሎች ትላልቅ ልቀቶችን የሚፈጽሙ ሃገራት በሃገራቸው ከሰልን በኃይል ምንጭነት መጠቀም መጨመርን ለማቆም ቁርጠኞች ካልሆኑ "ክፍተቶች" መኖራቸውን ተናግረዋል ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የከሰል አጠቃቀምን በመቀነስ ረገድ መሻሻል ቢታይም እአአ በ2019፣ 37 በመቶ የሚሆነውን የአለም ኤሌክትሪክ ከዚሁ ኃይል ምንጭ ይገኛል።

እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ፖላንድ እና ህንድ ያሉ ሃገራት የኃእል ዘርፋቸውን ታዳስ ለማድረግ ትልቅ መዋለ ነዋይ ያስፈልጋቸዋል።

በኮፕ26 የግሪንፒስ ልዑክ መሪ የሆኑት ጁዋን ፓብሎ ኦሶርኒዮ "ይህ መግለጫ አሁንም በዚህ ወሳኝ አስርት ዓመታት ውስጥ መጓዝ ከሚጠበቅበት ያነሰ ነው" ብለዋል ።

አክለውም "ስምምነቱ የሚያብረቀርቅ ርዕስ ቢሆንም ሃገራት መች ማጠናቀቅ እንዳለባቸው የራሳቸውን መርሃ ግብር እንዲመርጡ ትልቅ እድል የሚሰጥ ይመስላል" ሲሉ ገልጸዋል።