አሌክ ባልድዊን በፊልም ቀረጻ ላይ በድንገት የገደላት ባለሙያ "ጓደኛዬ ነበረች" አለ

ታትሟል

ታዋቂው የፊልም ተዋናይ አሌክ ባልድዊን በቅርቡ በነበረ የፊልም ቀረፃ ላይ የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯን ሃሊና ሁቺንስን በድንገት ተኩሶ ከገደለ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረ ሲሆን "ጓደኛዬ ነበረች" ብሏል።

ተዋናዩ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ በፊልም ፕሮዳክሽን ላይ የሚደረገውን የጦር መሳሪያ አጠቃቀም መገደብ እንደሚደግፍ ተናግሯል።

በምርመራው ዝርዝር ላይ የበለጠ መረጃ እንዳይሰጥም ፖሊስ ትዕዛዝ ማስተላለፉንም አስረድቷል።

አቃቤ ህግ 'ሴንቸሪ ዌስተርን ረስት' ፊልም ቀረፃ ላይው በተከሰተው ግድያ የወንጀል ክስ ሊመሰረት እንደሚችልም ከሰሞኑ አስታውቋል።

ተዋናዩ ባለማወቅ በተቀባበለ ሽጉጥ በተኮሰው ጥይት የ42 ዓመቷን የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯን በጥይት ሲገድል፤ ዳይሬክተሩን ደግሞ አቁስሏል።

መርማሪዎች እንደተናገሩት በቀረፃው ላይ ሽጉጡ ባዶ መሆን ቢኖርበትም ተቀባብሎ እንደነበር የሚጠቁሙ ፍንጮች እንዳገኙና በደህንነትም ዙሪያ አንዳንድ ቸልተኝነት ነበር ብለዋል።

"ጓደኛዬ ነበረች። የቀረፃው ቦታ ሳንታ ፌ በደረስኩበት የመጀመሪያ ቀን ከዳይሬክተሩ ጆኤል ጋር ሆነን አብረን እራት በልተናል" ሲል አሌክ ባልድዊን በቨርሞንት ግዛት እሱንና ቤተሰቡን ሲከታተሉ ለነበሩ ፎቶግራፍ አንሺዎች ተናግሯል።

"በጣም የምንቀራረብ የፊልም ቡድን አባላት ነበርን እናም ይህ አሰቃቂ ክስተት ተፈጠረ" ብሏል።

ተዋናዩ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ በቲኤምዜድ ድረገጽ ታትሟል። ባልድዊን ድንገተኛውንም አደጋ አስመልክቶም በጭራሽ መከሰት የሌለበትና ያልተለመደም ነው ብሏል።

"በፊልም ቀረፃ ወቅት ላይ የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን ለመገደብ የሚደረገው ጥረትም ላይ ትኩረት አደርጋለሁ" ሲል አክሏል።

የፖሊስ የመጀመሪያ ግኝቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሳንቴ ፌ ፖሊስ ኃላፊ አዳን ሜንዶዛ በበኩላቸው " በፊልም ቀረፃው ላይ ሌሎች የተቀባበሉ ሽጉጦች እንደነበሩ ጥርጣሬዎች አሉን" ብለዋል።

አክለውም "በፊልም ቀረፃው ላይ የተቀባበሉ ሽጉጦች እንዴት እንደነበሩ ለማወቅ እንሞክራለን። ምክንያቱም በስፍራው መገኘት አልነበረባቸውም" ሲሉም አክለዋል።

ፖሊስ እስካሁን 600 ማስረጃዎችን ማግኘቱን የተናገሩት ኃላፊው ከነዚህም መካከል ሶስት ሽጉጦች እና 500 ጥይቶች ይገኙበታል።

የፊልሙ መሳሪያ ተቆጣጣሪ ሃና ጉቴሬዝ-ሪድ ጠበቆች በበኩላቸው የተቀባበለው መሳሪያ ከየት እንደመጡ ደንበኛው እንደማታውቅ በዚህ ሳምንት መግለጫ አውጥተዋል።