ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በየመን ውዝግብ ሳቢያ ሳዑዲ አረቢያ የሊባኖስን አምባሳደር አባረረች
የሊባኖስ አንድ ሚኒስትር 'ስድብ' አዘል አስተያየት ሰንዝረዋል በሚል ሳዑዲ አረቢያ የሊባኖስ አምባሳደር በ48 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ አዛለች።
በተጨማሪም የሳዑዲ መንግሥት ከሊባኖስ የሚመጡ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ አገር እንዳይገቡ እገዳ ጥሏል። ከዚህም ባሻገር ሳዑዲ አረቢያ በቤሩት የሚገኘውን አምባሳደሯን "ለምክክር" እንደጠራችም ተናግራለች።
ለዚህ የሳዑዲ እርምጃ መነሻ የሆነው ከቀናት በፊት የሊባኖስ የማስታወቂያ ሚኒስትር በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የየመን ወታደራዊ ዘመቻን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ሲሆን፤ የተሰነዘረው አስተያየት የሳዑዲ መንግሥትን አስቆጥቷል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር የሳዑዲ ውሳኔ እንዳሳዘናቸው የገለጹ ሲሆን፤ ውሳኔያቸው በድጋሚ እንደሚያጤኑት ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
የሊባኖስ የማስታወቂያ ሚኒስትር ጆርጅ ኮርዳሂ ከወራት በፊት ተቀርጾ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተላለፈ ቃለ ምልልስ፤ በየመን ጦርነት ውስጥ ሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን አጥቂዎች ብለው ሲጠሯቸው ተደምጠዋል።
በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት በየመን ለሰባት ዓመታት የሀውቲ አማጽያንን ሲዋጋ ቆይቷል።
ኮርዳሂ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በሰጡት በዚያ ቃለ ምልልስ ግጭቱን "እርባና ቢስ" ያሉት ሲሆን የሀውቲዎች እንቅስቃሴ "ራስን የመከላከል" ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በየመን ተፈጽመዋል በተባሉት የግፍ ድርጊቶች ሳዑዲ አረቢያም ሆነ አማጺያኑ ወቀሳዎች ተሰንዝሮባቸዋል። ሆኖም የሊባኖስ መንግሥት አቋሙ ግልጽ አይደልም ብለዋል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ።
በሊባኖስ እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለው ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል። በሌላ በኩል በኢራን የሚደገፈው ሂዝቦላህ እንዲሁም የሀውቲ እንቅስቃሴ የተጠናከረ መሠረት እየያዘ መምጣቱ ይነገራል።
ታዲያ ሳዑዲን ያስቆጣውን አስተያየት የሰነዘሩት ኮርዳሂ፤ ከሂዝቦላህ ጋር የተቆራኘ የፖለቲካ ቡድን አባል ናቸው።
የሳዑዲ መንግሥት ውሳኔ በተሰማ በስዓታት ውስጥ ባህሬን ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች። የሊባኖስን አምባሳደር ከአገሯ እንዲወጣ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።
ከከፋ የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና ከፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር እየተጋፈጠች የምትገኘውን ሊባኖስ እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ በሳዑዲ ውሳኔ "በጣም ማዘናቸውን" እና ግንኙነታቸውን ለማስተካከል እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
"መፈታት ያለባቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረታችንን እንቀጥላለን" ሲሉም ተደምጠዋል።
በሳዑዲ የተወሰደው እርምጃ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከዚህም ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይወስደው ተሰግቷል።
ሳዑዲ ለወሰደችው እርምጃ የማስታወቂያ ሚኒስትሩን አስተያየት መነሻ ታድርግ እንጂ የሳዑዲ ዋነኛ ቅሬታ በሊባኖስ ሄዝቦላህ የበላይነት እያደገ መምጣቱ እንደሆነ ይነገራል።
ሄዝቦላህ በኢራን የሚደገፍ እና በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀ የሺዓ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ሳዑዲ የዚህን ቡድን የበላይነትን እንደማትፈልግ ይነገራል።