የጃፓኗ ልዕልት "ተራ" ሰው በማግባቷ ማዕረጓንና የ1.3 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ማጣቷ ተገለጸ

ኬሪ ኩሞሮና ልዕልት ማኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የጃፓኗ ልዕልት ማኮ የኮሌጅ ፍቅረኛዋን ኬይ ኮሙሮን አግብታለች - በዚህም የልዕልትነት ማዕረጓን አጥታለች።

በጃፓን ህግ መሰረት ሴቶች የንጉሳውያን ቤተሰቦች አባላት "ተራ" ከሚባል ሰው ጋር የጋብቻ ስነ ስርዓት ከፈፀሙ ያላቸውን ማዕረግ ያጣሉ።

የስርወ መንግሥቱም አባል አይሆኑም። ይህ ሁኔታ ግን ለወንድ አባላቶቹ ተፈፃሚ አይሆንም።

የቀድሞዋ ልዕልት በተለመደው ሞቅ ደመቅ ባለ ንጉሣዊ ሰርግ አልተሞሸረችም እንዲሁም የቤተሰቡ አባላት ሲዳሩ የሚቀርበውን የ1.3 ሚሊዮን ዶላር ክፍያም ውድቅ አድርጋለች።

በዚህም በንጉሳዊ ስነ ስርዓት ባለማግባትም ሆነ ገንዘብ ባለመቀበል የመጀመሪያዋ ሴት የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሆናለች።

ጥንዶቹ ኑሯቸውን ወደ አሜሪካ - ባለቤቷ ኮሙሮ በጠበቃነት ወደሚሰራበት - ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የልዕልቷን ውሳኔ ከዩናይትድ ኪንግደም ንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ሜጋን መርክል እና ልዑል ሃሪ ትዳር ጋር ብዙዎች አነፃፅረውታል።

ይህም "የጃፓኑ ሃሪ እና ሜጋን" የሚል ቅጽል ስም አስገኝቶላቸዋል።

እንደ ሜጋን መርክል ከተራ ቤተሰብ ነው የተወለደው የተባለው ኮሙሮ የልዕልቲቷ ግንኙነት ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ውግዘት ደርሶበታል።

በርካቶች ከፍተኛ ክትትል የሚያደርጉባቸው ሲሆን በቅርቡም ከፈረስ ስፖርት ውድድር ጋር በተያያዘ በስፖርታዊ ጨዋነት ተወቅሷል። አንዳንዶችም የፀጉር አቆራረጡ ልዕልት የሚያገባ ሰው ደረጃ የለውም በሚልም ተችተውታል።

ልዕልት ማኮ ትዳሯን ለማስመዝገብ ማክሰኞ በአገሬው አቆጣጠር 10፡00 ሰዓት አካባቢ ለወላጆቿ ፉሚሂቶ እና ኪኮ በተደጋጋሚ እጅ ነስታ የወላጆቿን ቤት ትታ ወጥታለች።

በተጨማሪም ልዕልቲቷ ከመውጣቷ በፊት ታናሽ እህቷን አቅፋ ተሰናብታለች ሲል ኪዮዶ የዜና አውታር ዘግቧል።

ጥንዶቹ ማክሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡና አስቀድሞ ለቀረቡ አምስት የተመረጡ ጥያቄዎች አጭር የመክፈቻ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የጃፓኗ ልዕልት ፍቅርን በመምረጧ ከስርወ መንግሥቱ እንድትወጣ ተደርጋለች።