ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 መነሻን የሚያጣራ የመጨረሻ እድል ያለውን ግብረ ኃይል አቋቋመ
የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ የኮሮናቫይረስ ትክክለኛ መነሻን ለማረጋገጥ የመጨረሻው እድል ነው ያለውን አዲስ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን አሳወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት 26 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን የኮሮናቫይረስ መነሻ ምን እንደሆነ እንዲያጣሩ ሰይሟል።
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ በኋላ የቫይረሱ ትክክለኛ መነሻ ሳይታወቅ ቆይቷል።
ይህ በዓለም ጤና ድርጅት የተዋቀረው ቡድን ቫይረሱ በቻይናው ዉሃን የገበያ ቦታ ከእንስሳት ወደ ሰው ስለመታላለፉ አልያም ከላብራቶሪ አምልጧል ስለመባሉ ያጣራል ተብሏል።
ቻይና በተደጋጋሚ ቫይረሱ ከላብራቶሪ አምልጦ ወጥቷል የሚለውን መላ ምት በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች።
ከዘጠኝ ወራት በፊት ወደ ቻይና አቅነቶ የነበረ ሌላ የዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪ ቡድን የቫይረሱ መነሻ የሌሊት ወፎች ሳይሆኑ አይቀርም ብሎ ነበር። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ ግን ያስፈልጋል ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የቫይረሱን መነሻ ለማጥናት የተሰማራው ቡድን በቂ መረጃ መሰብሰብ አለመቻሉን እና ከቻይና መንግሥት ግልጽነት የሰፈነበት ትብብር ማግኘት አለመቻሉን በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ዋና ዳይሬክተሩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ትክክለኛ መነሻ ማወቅ ወደፊት ተመሳሳይ ወረርሽኞች እንዳይከሰቱ መከላከል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ዳይሬክተር ማይክል ራይን ይህ ቡድን የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ሁለት ዓመታት ለመድፈን የተቃረበው እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገው የኮቪድ-19 መነሻ ምን እንደሆነ ለማወቅ የተደረጉ ጥረቶች አጥጋቢ ውጤቶች አለማምጣታቸው የሚታወቀስ ሲሆን ከዚህ ቀደም የተከሰቱት ወረርሽኞች ግን መነሻቸውን ለማወቅ ረዥም ጊዜ አልፈጀም ነበር።
ከዚህ ቀደም የተከሰቱት ወረርሽኞች በሙሉ መነሻቸው ከእንስሳት ነበር።
ከዘጠኝ ወራት በፊት ወደ ቻይና ያመራውም የዓለም የጤና ቡድን የኮሮናቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰዎች ሳይተላለፈ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለው። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ከላብራቶሪ ነው የወጣው በሚለው መላ ምት የሚያምኑ በርካቶች ናቸው።