ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍጋኒስታን መስጊድ በጸሎት ወቅት በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 30 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ
በአፍጋኒስታን ካንዳሃር ከተማ በሚገኝ መስጊድ በዛሬው ዕለት በደረሰ ፍንዳታ ከ30 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 90 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ፍንዳታው የደረሰው የሺዓ ማህበረሰብ በሚያዘወትሩት መስጊድ ሲሆን በወቅቱም በአምልኮ ስርዓት ላይ መሆናቸው ተዘግቧል።
ፍንዳታው ከደረሰበት ቢቢ ፋጢማ ከተሰኘው መስጊድ የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት የተሰባበሩ መስኮቶች እና ወለል ላይ የተንጋለሉ አካላት የታዩ ሲሆን ሌሎች ምዕመናንም ለመርዳት ሲሞክሩ ያሳያል።
የፍንዳታው መንስኤ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ሳይሆን እንዳልቀረ ተጠርጥሯል።
የአይን እማኞች እንደገለጹት ሶስት ፍንዳታዎች የተከሰቱ ሲሆን አንደኛው በዋናው በር ላይ፣ ሌሎቹ ደግሞ ምዕመኑ በሚታጠብበት አካባቢ ነው ተብሏል።
በእልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ አርብ ቀን ምዕመናን በመስጊድ ተሰብስበው የሚፀልዩበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች ነበሩ።
ቢያንስ 15 አምቡላንሶች በቦታው እንደነበሩ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋዜጠኛ ተናግሯል።
የታሊባን ልዩ ኃይሎች የቦታውን ደህንነት አስጠብቀው ተጎጂዎችን ለመርዳት ሰዎች ደም እንዲለግሱ መጠየቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቢቢሲ የአፍጋኒስታን ዘጋቢ ሴክደርደር ከርማኒ እንደሚለው አይ ኤስ-ኬ የተባለው የአከባቢው የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ቅርንጫፍ ከጥቃቱ በስተጀርባ ነው ተብሎ እንደሚገመት ተናግሯል።
ካንዳሃር የአፍጋኒስታን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ እና የታሊባን መንፈሳዊ የትውልድ ቦታ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የታሊባን ጠላት የሆነው አይኤስኬ የሚፈፅመው ጥቃት ጉልህ ነው።
ባለፈው ዓርብ በሰሜናዊ ኩንዱዝ ከተማ አርብ ዕለት በሌላ የሺዓ መስጊድ ላይ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል። አይ ኤስ-ኬ ጥቃቱን እንደፈጸመ ያስታወቀ ሲሆን ይህም የአሜሪካ ወታደሮች ከወጡ በኋላ የከፋ ጥቃት ነው ተብሏል።
የሱኒ ሙስሊም ቡድን የሆነው አይ ኤስ-ኬ ፣ ፣ በአፍጋኒስታን ካሉ የጂሃዲስት ተዋጊ ቡድኖች ሁሉ እጅግ ጽንፈኛ እና ብዙ ጥቃቶችንም የሚያደርስ ነው።
የሱኒ ሙስሊም አክራሪዎች መናፍቃን አድርገው በሚመለከቷቸው የሺዓ ሙስሊሞች ላይ አነጣጥረዋል።
አይ ኤስ ኬ ኬ የአፍጋኒስታን የፀጥታ ሀይሎችን ፣ ፖለቲከኞችን እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ፣ ታሊባንን ፣ ሺዓ ሙስሊሞችን ፣ የአሜሪካን እና የኔቶ ሀይሎችን እና የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎችን ኢላማ አድርጓል።
ታሊባን ከአሜሪካ ጋር የተስማማውን ስምምነት ተከትሎ የውጭ ኃይሎች ከሀገሪቱ ከወጡ በኋላ አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሯል።
በአውሮፓውያኑ 2001 የአሜሪካ ወታደሮች ታሊባንን ከስልጣን ካስወገዱ ከሁለት አስርት አመታት በኋላም ወደ ስልጣን ተመልሷል።