ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍሪካ ከ85 በመቶ በላይ የኮቪድ-19 ህሙማን በምርመራ አለመለየታቸው ተነገረ
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ከሚያዙ ሰዎች አብዛኞቹ በምርመራ ሳይታወቁ እንደሚቀሩ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
ድርጅቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በአህጉሪቱ ውስጥ በበሽታው ከተያዙ ሰባት ሰዎች መካከል ስድስቱ ተመርምረው ያልተለዩ ናቸው።
እዚህ አሃዝ ላይ የተደረሰው በአህጉሪቱ ውስጥ በበሽታው ምክንያት የተመዘገቡትን ሞቶች እና በወረርሽኙ ከተያዙት ሰዎች መካከል ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ምጣኔን በማስላት ነው።
አስካሁን ድረስ አፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር ስምንት ሚሊዮን ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ግን ትክክለኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 59 ሚሊዮን ነው ይላል።
በአህጉሪቱ አስካሁን የበሽታውን ምርመራ ያደረጉ ሰዎች የወረርሽኙ ምልክቶችን አሳይተው ወደ ጤና ተቋማት የሄዱና ከአገር ውጪ ለመጓዝ የግድ ምርመራ መድረግ ያለባቸው ናቸው።
ይህ ማለት ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበሽታውን ምልክት ሳያሳዩ ወረርሽኙን የሚያስተላልፉ ሰዎች በሕብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ሳይታወቅ ቫይረሱን እያስፋፉት ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ አመልክቷል።
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በሚቀጥለው ዓመት በፈጣን የምርመራ አገለግሎት ሰባት ሚሊዮን ሰዎችን ለማዳረስ በስምንት የአፍሪካ አገራት ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት የማኅበረሰብ ምርመራን እያጠናከረ ነው።
"በውስን የበሽታው ምርመራ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እንዲሁ በጭፍኑ እየተፍጨረጨርን ነው... የምርመራው ቁጥር ሲጨምር ፈጣን ልየታ፣ ዝቅተኛ የበሽታው መስፋፋት እና በሚወሰድ የተለየ እርምጃ በርካታ ህይወትን ማዳን ይቻላል" ሲሉ የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ ተናግረዋል።
ቡሩንዲ፣ አይቮሪኮስት፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ሞዛምቢክ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሴኔጋል እና ዛምቢያ የዓለም ጤና ድርጅት የምርመራ ዕቅዱን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው አገራት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ ውስጥ የሚመዘገበው የህሙማን ቁጥር መቀነስ ያሳየ ቢሆንም ያለው ዝቅተኛ የክትባት መጠን ወረርሽኙ በበርካታ አገራት ውስጥ ስጋት ሆኖ እንደሚቆይ ድርጅቱ ገልጿል።