የዓለም ጤና ድርጅት የእርዳታ ሠራተኞች በኮንጎ በወሲብ ብዝበዛ መሳተፋቸው አሳሰቦኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተቀስቅሶ የነበረውን የኢቦላ ወረርሽኝን ለመግታት ተሰማርተው በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ካደረሱ 83 የእርዳታ ሠራተኞች መካከል የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞች እንደሚገኙበት አንድ ሪፖርት አመለከተ።
ዘጠኝ የአስገድዶ መድፈር ክሶችን ያካተተው ይህ በደል እአአ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ የደረሰ ሲሆን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ሠራተኞች የተፈጸመ ነው።
ሪፖርቱ ይፋ የተደረገው ከ50 በላይ የአካባቢው ሴቶች የወሲብ ጥቃት እንደተፈጸማቸውን ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ነው።የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጉዳዩን "ይቅርታ የማያሰጥ" ሲሉ ገልጸውታል።
ባለ 35 ገጹ ይህ ሪፖርት ምርመራ ከተደረገ በኋላ በገለልተኛ ኮሚሽን የተዘጋጀ ነው።
ሥራ ለማግኘት በልዋጩ ወሲብ እንዲፈፅሙ እንደተገደዱ የገለጹ በርካታ ሴቶችን ቃለ መጠይቅ ያደረገው ኮሚሽኑ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት 83 ሰዎች መካከል 21ዱ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀጥረው እንደሚሠሩ አረጋግጧል።
በተጨማሪም የአካባቢው ሴቶች መጠጥ ጠጥተዋል፣ በሆስፒታሎች ውስጥ "በደፈጣ" ተጠቅተዋል፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም ተገደዋል እንዲሁም ሁለቱ አርግዘዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን በድርጅቱ ተቀጥረው የሚሠሩ የአራት ሰዎችን ውል ያቋረጠ መሆኑን ገልጾ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ቃል ገብቷል።
ማክሰኞ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ ለተጎጂዎች እና ከጥቃቱ ለተረፉት በቀጥታ ይቅርታ ጠይቀዋል።
"እናንተን ለማገልገል እና ለመጠበቅ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀጥረው በሚሠሩ ሰዎች በደረሰባችሁ ነገር አዝናለሁ። ወንጀለኞቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ሳይሆን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሬ ነው" ብለዋል።
በመጨረሻም ኃላፊነቱ እሳቸው ላይ እንደሆነ እና ተጎጂዎችን ለመደገፍ እና ለመጠበቅ እንደሚረዱ ቃል የገቡ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትን መዋቅር እና ባህል ለማስተካከልም ቃል ገብተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞዬቲም "በሠራተኞቻቸው ድርጊት" ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ይቅርታ ጠይቀዋል።
ግኝቶቹንም "አስፈሪ እና ልብ ሰባሪ" ብለውታል።
ኮሚሽኑ በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሃገር የጾታ ብዝበዛ እና የመብት ጥሰቶችን አደጋዎች ለመቆጣጠር "ግልጽ የመዋቅር ውድቀቶች እና የዝግጁነት ማነሶችን" እንዳገኘ ገልጿል።
በከፊል ይህ የሆነው ኢቦላን ለማጥፋት ትኩረት ስላለ ነው ብሏል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ ከ2,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ስርጭቱን ለመግታት ዓለም አቀፍ ጥረቶችን የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የወረርሽኙ ማብቃት አስታውቋል።












