ሀሽፐፒ፡ ሚሊዮን ዶላሮችን ያጭበረበረው የኢንስታግራም ኮከብ

የፎቶው ባለመብት, hushpuppi
የመዝገብ ስሙ ራሞን አባስ ነው። 2.5 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮቹ ግን 'ሀሽፐፒ' በሚለው ስሙ ነው የሚያውቁት። የሀሽፐፒ ኢንስታግራም ሕይወት የቅንጡ ነው።
ተከታዮቹ ሀሽፐፒን የሚያውቁት ቤተ-መንግሥት በመሰል ቤቱ ሲኖር፣ እጅግ ውድ መኪና ሲያሽከረክር እና በግል አውሮፕላን ሲበር ነው።
የአሜሪካው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ግን ሀሽፓፒን አደገኛ አጭበርባሪ እና በወንጀል የሚፈለግ ግለሰብ እንደሆነ ነው የሚያውቀው።
ናይጄሪያዊው ሀሽፐፒ ባለፈው ዓመት ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ አሁን በአሜሪካ እስር ቤት ይገኛል። ሀሽፐፒ በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኝነቱን አምኖ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራትን ሊከናነብ ጫፍ ደርሷል።
የቀረቡበት ክሶች ደግሞ ማጭበርበር፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ ማስመሰል የሚሉ ይገኙበታል።
"ያሁ ቦይስ"
የ37 ዓመቱ ሀሽፐፒ ትውልድ እና እድገቱ በናይጄሪያዋ ትልቅ ከተማ ሌጎስ ውስጥ በሚገኝ የድሆች መንድር ውስጥ ነው።
የሌጎስ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሴዬ፤ አባስ ገና ልጅ እያለ አስታውሰዋለሁ ይላል። ሴዬ እንደሚለው ሀሽፐፒ ልጅ ሳለ ወላጅ እናቱን ገበያ ውስጥ ያግዝ ነበር። ወላጅ አባቱ ደግሞ የታክሲ ሾፌር ነበሩ።
ሀሽፐፒ እየጎረመሰ ሲሄድ የሚያገኘውን ገንዘብ ባገኘበት ይበትን ነበር ይላል ሴዬ። "በጣም ደግ ነበር። አካባቢው ላሉ በሙሉ ቢራ ይገዛ ነበር" በማለት ያስታውሰዋል።
ሁሉም ሰው፤ ግን ሀሽፐፒ ቢራ የሚጋብዝበትን ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ያውቅ ነበር - ከሳይበር ወንጀል (በበየነ መረብ አማካኝነት የሚፈጸመው ወንጀል)። ሀሽፐፒ "ያሁ ቦይስ" ከሚባሉት መካከል ነበር ይላል።
"ያሁ ቦይስ" አታላዮች ናቸው። የፍቅር አታላይ። በኢ-ሜይል የሚያገኟቸውን 'ፍቅር ይዞኛል' እያሉ በመጻፍ የሚያታልሉ። መጠሪያቸውንም ያገኙት በወቅቱ በርካታ ተጠቃሚዎች ከነበሩት ያሁ ሜይል ነው።
አዴዴጂ ኦዬንጉ በሌጎስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ወንጀል ባለሙያ ናቸው። 'ያሁ ቦይስ' ሐሰተኛ ማንነትን በመያዝ በኢሜይል አማካኝነት የፍቅር ግንኙነት ይጀምራሉ። ከዚያም ከአፍቃሪያቸው ገንዘብ ያስልካሉ በማለት የአታላዮችን ማጭበርበሪያ ዘዴ ያስረዳሉ።
እንደ በርካታ የናይጄሪያ 'ያሁ ቦይስ' አባስም የወንጀል አድማሱን አሰፋ። በርካቶች ወደ ሩቅ ምሥራቋ ማሌዢያ ሄዱ። አባስም ተከትሏቸው እአአ 2014 ኳላ ላምፑር ገባ፤ እአአ 2017 ላይ ደግሞ ዱባይ ከተመ።

የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች
በዚህ ወቅት ነበር ኢንስታግራም ላይ የሚለጥፋቸው ቅምጥል ህይወቱን የሚያሳዩ ፎቶዎቹ እና የማችበርበር ወንጀሎቹ ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ ያሉት።
እአአ 2019 መጀመሪያ ላይ ሀሽፐፒ በሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ማልታ ውስጥ ከሚገኝ ባንክ የተሰረቀን 15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ለማስመሰል ሙከራ አድርጎ የነበር።
ነገር ግን ከፍ ያለ ገንዘብ ያስገኝልኛል ያው ሙከራው እንዳሰበው ሊሳካለት ሳይችል ቀረ።
ሀሽፐፒ ውጥኑ አለመሳካቱን ሲረዳ ለጓደኛው፤ "ወይኔ" ሲል በቁጭት ያሰፈረውን የጽሑፍ መልዕክት ልኮለት እንደ ነበር ፖሊስ ከሀሽፐፒ ስልክ መረጃ ይዟል።
በተጨማሪም ሀሽፐፒ፤ "ቀጣዩ ሥራ [ሌላ ማጭበርበር] ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው። ዝግጁ ሲሆን አሳውቅሃለሁ። ማወቃቸው መጥፎ ሆነ እንጂ ጥሩ ጨዋታ ነበር" የሚል ይዘት ያለው የጸሑፍ መልዕክት ልኮ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, hushpuppi
ሐሰተኛው የኢ-ሜይል አድራሻ
የእአአ 2019 መጨረሻ ወራት ላይ አባስ በሜክሲኮ የባንክ ሒሳብ ደብተር ከፈተ።
ይህ የሆነው ስሙ ካልተጠቀሰ ከአንድ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ክለብ 100 ሚሊዮን ፓዎንድ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ካለ ኩባንያ 200 ሚሊዮን ፓዎንድ ክፍያ ለመቀበል ነበር። የእግር ኳስ ክለቡም ሆነ የኩባንያው ስም በፍርድ ቤት ሰነድ ላይ አልተጠቀሰም።
ይህ የማጭበርበር ዘዴ የታቀደው ከኩባንያ ኢ-ሜይል ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሐሰተኛ የኢ-ሜይል አድራሻ ሐሰተኛ መረጃ በመስጠት ነው።
የኢ-ሜይል መልዕክቱ የተላከ የሚመስለው ከትክክለኛው የኩባንያ ኢ-ሜይል አድራሻ ነው። ነገር ግን አንዲት ፊደልን ወይም ቁጥርን ይቀይራሉ።
በዚያ የኢ-ሜይል መልዕክት ላይ ሀሽፐፒ እና ግብረ አበሮቹ አገልግሎት አቅራቢ መስለው በመቅረበ የባንክ ለውጥ ስላደረጉ ክፍያ የሚፈጸምበት ባንክ አድራሻ እንዲቀየር ጠየቁ።
የሒሳብ ክፍል ሠራተኛ የቀረበለትን የክፍያ ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ። ኩባንያው ከዩናይትድ ኪንግደም ሜክሲኮ ለሚገኝ የባንክ ሒሳብ ከፍያ አልፈጽምም በማለቱ እንጂ የእነ ሀሽፐፒ ሴራ ሊሳካ ይችል ነበር።
በሌሎች አጋጣሚዎች ግን ይህንን ዘዴ በመጠቀም ሀሽፐፒ በርካቶችን አጭበርብሯል። በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያሉ ስምንት የእንግሊዝ ዜጎች በሀሽፐፒ ተጭበርብረናል ሲሉ ከስር መስረተዋል።

የፎቶው ባለመብት, hushpuppi
የኳታር ትምህር ቤት መጭበርበር
አባስ የዛሬ ዓመት ገደማ ዱባይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት በኳታር ከሚገነባ ትምህርት ቤት ጋር በተያያዘ በርካታ ገንዘብ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከአንድ የኳታር ዜጋ ላይ አጭበርብሯል።
ለዚህ የማጭበርበር ተግባሩ ሀሽፐፒ ተበዳዩን ለማታለል በኒው ዮርክ ያለ የባንክ ባለሙያ መስሎ ቀርቧል። በባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር ትምህር ቤት ለመገንባታ የኳታሩ ዜጋ 15 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈልጓል።
ይሁን እንጂ በሦስት ወራት ውስጥ ሀሽፐፒ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና አሜሪካ ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን ከተበዳዩ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተቀብለዋል።
ሀሽፐፒ ላይ የቀረበው የክስ ወረቀት እንደሚያሳየው ከተበዳዮቹ ያጭበረበረው ጠቅላላ ገንዘብ ወደ 24 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል። አንዳንዶች ግን ገንዘቡ ከዚህም በላይ ነው ይላሉ።
ምንም እንኳ ሀሽፐፒ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ መጠቀም በሚል በቀረበበት ክስ ጥፋተኝነቱን ቢያምንም፤ ዛሬም ድረስ የኢንስታግራም ገጹ ክፍት እንደሆነ ነው። የተከታዮቹ ቁጥርም እየጨመረ ነው።
ለቀረበበት የወንጀል ክስ ጥፋተኝነቱን ያመነው ግለሰብ ገጽ ለምን ክፍት እንዲሆን ተደረገ ሲል ቢቢሲ ለኢንስታግራም ጥያቄ አቅርቦ ነበር። "ኢንስታግራም ምርመራ አድርጌ ገጹን መዝጋት አላስፈለገኝም" ብሏል።
በሌጎስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ወንጀል ባለሙያው ሀሽፐፒን እንደ አርአያ አድርገው የሚቆጥሩት መብዛታቸው አሳስቧቸዋል።
"በርካታ ወጣቶች ብዙ መከራ በሚያዩበት አገር ውስጥ ነን። እንደነሱ የነበረ ልጅ በሀብት ማማ ላይ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መድረሱን ያያሉ። ልጆቻቸው ያሁ ቦይስ እንዲሆኑ የሚያስተምሩ ወላጆችም አሉ" በማለት ይናገራሉ።












