የሰሜን ኮሪያ የረዥም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ለምን የዓለም ስጋት ሆነ?

የረዥም ርቀት ሚሳይል

የፎቶው ባለመብት, KCNA

የምስሉ መግለጫ, የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አዲስ የተሞከረውን ክሩዝ ሚሳይል ምሥል አውጥቷል
ታትሟል

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሰሜን ኮሪያ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን አስታውቃለች። ረዥም ተወንጫፊ ሚሳኤል የጃፓንን አብዛኛውን ክፍል መምታት የሚያስችል ነውም ተብሏል።

ረዥም ርቀት የሚወነጨፈው ሚሳኤል ከባልስቲክ ሚሳኤል በተለየ መልኩ አቅጣጫቸውን በመለዋወጥ ከማይጠበቅ ማዕዘን ለማጥቃት የሚያስችል ነው።

ይህም ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመተኮስ በጣም በርካታ እና የተራቀቁ ዘዴዎችን እንደምትከተል ያሳያል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ተፈጥሯዊ አደጋዎች እና ውስጣዊ ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ሰሜን ኮሪያን ለመሠረታዊ የኑክሌር መከላከያ ግንባታ ቅድሚያ ከመስጠት አላገዳትም።

በቅርብ ጊዜ ያደረገችው የተሳካ ሙከራ ግን ጥያቄዎችን አስከትሏል። ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወቅት ለምን ማስወንጨፍ አስፈለጋት? ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ለዚህ ቅድሚያ መስጠቷስ የሚነግረን ምንድን ነው? የሚሉት ከጥያቄዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ፕዮንግ ያንግ

ሰሜን ኮሪያ እአአ ከ2019 ጀምሮ በጥራትም በብዛትም የተሻሻለ የኑክሌር አቅሟን እያሰፋች ነው።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እአአ በ2019 የካቲት ወር ላይ በቪየትናም ሃኖይ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ካደርጉት ያልተሳካ ጉባዔ ከተመለሱ በኋላ በሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መከላከያ ግንባታቸውን ለመቀጠል እና በራሱ የሚተማመን ብሔራዊ የመከላከያ ስትራቴጂ ለመከተል ወስነዋል።

ነገር ግን ሰሜን ኮሪያ በምግብ እጥረት እና በከፋ የምጣኔ ሐብት ቀውስ እየተናጠች ይህንን ለማድረግ ለምን መረጠች? በርካቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።

ከውስጣዊ ሁኔታዋ አንጻር ብንመለከት አገሪቷ የምታደርጋቸው የሚሳኤል ሙከራዎች ብሔራዊ መከላከያን ስለመገንባት፣ ራስን ስለመቻልና ሞራል ግንባታን የተመለከቱትን የኪም ትርክቶችን ያጎላሉ።

ይህን በተግባር ስንመለከተው የእነዚህ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አዲስ አቅም፤ ከአዳዲስ አቅም ጋር መታገል ያለባቸውን የሰሜን ኮሪያ ተቃዋሚዎችን እቅድም ያወሳስባሉ።

ከባልስቲክ ሚሳኤሎች በተቃራኒ ክሩዝ ሚሳኤሎች ወደ ኢላማቸው የሚጓዙት ቀስ ብለው ነው።

ሰሜን ኮሪያ በቅርብ የሞከረችው ክሩዝ ሚሳኤል በሁለት ሰዓታት የበረራ ጊዜ 1500 ኪሎ ሜትር ርቀት ይጓዛል።

ባሊስቲክ ሚሳኤል ግን ይህን ያህል ርቀት ለመጓዝ የሚወስድበት የደቂቃዎች ጊዜ ነው።

ሰሜን ኮሪያ በዚህ ክሩዝ ሚሳኤል ላይ ፍላጎት ያሳደረችው በተቃዋሚዎቿ አስቸጋሪነት ሳቢያ ሊሆን ይችላል።

እነዚህ ሙከራዎችም የሚያሳዩት ምንም እንኳን ኪም አገራቸው የገጠማትን ችግር እየታገሉ ቢሆንም የኑክሌር አቅሟን ለማሳደግ አሁንም ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው።

በመሆኑም በሰሜን ኮሪያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ካልታየ ወይም በአሜሪካ የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካልተደረገ በስተቀር ፒዮንግያንግም አቅሟን ማሻሻል እና ማጠናከሯን እንደምትቀጥል ይጠበቃል።

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወቅት ይህንን የሚሳል ሙከራ ማድረግ ለምን መረጠች?

ምንም እንኳን በዚህ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ቢሰጡም የዚህ ሚሳኤል ትውውቅ እና ሙከራ ከባይደን አስተዳዳር ፖሊሲዎች ወይም ከመስከረም 11ቀኑ ጥቃት 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ጋር ብዙም ግንኙነት የላቸውም።

ኑክሌር የመሸከም አቅም

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን 'ስትራቴጂካዊ' መሣሪያዎች ያላቸው እነዚህ አዲስ የተሞከሩ ሚሳኤሎች ለደቡብ ኮሪያ ፣ ለጃፓን እና ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አሳሳቢ ሆነዋል።

ከዚህ ቀደም በሰሜን ኮሪያ የክሩዝ ሚሳኤል አንድም የኑክሌር የጦር መሣሪያ አቅርቦት ሚና አልነበረውም።

ነገር ግን የዚህ ሚሳኤል መበልፀግ እንደ ድንገት የመጣ አይደለም። ኪም ባለፈው የፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ እንዲህ ዓይነት ሥርዓት እያበለፀጉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ኪም ይህ የሚሳኤል ሥርዓት ወደፊት ለኑዩክሌር ጦር መሣሪያ አቅርቦት ሊያገለግል እንደሚችል አመልክተዋል።

ስለዚህ ሚሳል የምናውቀው ምንድን ነው?

ክሩዝ ሚሳኤሎች በአገልግሎታቸው ከባልስቲክ ሚሳኤሎች ይለያሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እንዳትሞክር ይከለክላል። ነገር ግን የሚከለክለው በዚህ ሳምንት የሞከረችውን ክሩዝ ሚሳኤልን አይደለም።

ምክንያቱ ደግሞ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ትልቅ እና ኃይለኛ የሆኑ ጭነቶችን መሸከም ስለሚችሉ፣ ረዥም ርቀት ስለሚጓዙና ፈጣን በመሆናቸው የበለጠ አስጊ እንደሆኑ ስለሚታሰብ ነው።

ነገር ግን የመጨረሻ መዳረሻቸው ላይ የመንቀሳቀስ ውስን አቅም ካላቸው ከባልስቲክ ሚሳኤሎች ይልቅ ክሩዝ ሚሳኤሎች ወደ ምድር ሲወርዱ ወደ ተለያየ አንግል በመዟዟር እና በጉዟቸውም በመዘዋወር ካልተጠበቁ ማዕዘኖች ለማጥቃት ያስችላሉ።

መሬት ላይ ያሉ የራዳር ሥርዓቶችም ብዙውን ጊዜ እነዚህን ሚሳኤሎች የሚያገኟቸው በጉዟቸው መጨረሻ ላይ ነው። ይህ ደግሞ እነርሱን ለመጥለፍ የመሞከር እድሉ በጣም ዝቅተኛ የሚሆንበት ደረጃ ነው።

በእርግጥ ክሩዝ ሚሳኤል ለሰሜን ኮሪያ በመሠረታዊነት አዲስ ቴክኖሎጂ አይደለም። ለዓመታት ከሶቭየት የመነጩ ፀረ መርከብ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ሞክራለች፤ አሻሽላለችም።

በቅርቡ የተሞከሩት ሚሳይሎች ግን ቀድሞ ከነበረው ክሩዝ ሚሳይሎች በመጠናቸው ይለያሉ። እነዚህ ክሩዝ ሚሳይሎች ሰሜን ኮሪያ በዘርፉ ያደረገችው ሰፊ ጥረት አንድ አካል ናቸው።

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር በቅርቡ እንደገመገሙት ፕዮንግያንግም የጋዝ ግራፋይት ሥራዋን በዮንግብዮን ኮምፕሌክስ እንደገና ጀምራለች።

ይህም ለኑክሌር ጦር መሣሪያ የሚውለውን ፕሉቶኒየም ማምረት መጀመሯን ያሳያል።

የክሩዝ ሚሳይል ሙከራ ከተደረገ በኋላ ባሉት ቀናት የባልስቲክ ሚሳይሎች ሙከራ ማድረጓ ሰሜን ኮሪያ ዘላቂነት ያለው ሚሳይል የማበልፀግ፣ የመሞከርና የመገምገም ዘመቻዎችን እንደገና መጀመሯን አመላክቷል።