ሰንበሬ ክብረ ወሰን ስታሻሽል ማራቶን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ ውጤቱ ተሰረዘበት

አትሌት ሰንበሬ ውድድሩን ካሸነፈች በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Alexander Hassenstein

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሰንበሬ ውድድሩን ካሸነፈች በኋላ
ታትሟል

እሁድ ዕለት ጀርመን ውስጥ በተካሄደ ውድድር አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የ5 ኪሎ ሜትር ክብረ ወሰንን ስታሻሽል ኦስትሪያ ቬይና በተደረገው ማራቶን ያሸነፈው ደራራ ሁሪሳ ያልተፈቀደ ጫማ አድርጎ በመሮጡ ውጤቱ ተሰረዘበት።

አትሌት ሰንበሬ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድሯን ከዚህ ቀደም በኬንያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቼፕኮኤች በ14፡44 ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን 14፡30 በሆነ ሰዓት ማሻሻል ችላለች።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ 5ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃ የነበረችው አትሌት ሰንበሬ ከውጤቱ በኋላ "በጣም ደስታ ተሰምቶኛል" ያለች ሲሆን፤ "ከኦሊምፒክ በኋላ ይህን የዓለም ክብረ ወሰን ማሻሻል እንደምችል ገብቶኛል" ማለቷን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ትናንት ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቲሮፕ ጀርመን ውስጥ በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችላለች።

አትሌት አግነስ በሞሮኮ አትሌት አሰማኤ ሌግህዛኦዩ ከ19 ዓመት በፊት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በ28 ሰከንዶች በማሻሻል 30፡17 በሆነ ሰዓት ውድድሯን አጠናቃለች።

አትሌት ደራራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ደራራ ውድድሩን ካሸነፈ ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የውድድር ደንብን በመጣሱ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ተነግሮታል።

ያልተፈቀደ ጫማ

እሁድ መስከረም 02/2014 ዓ.ም ኦስትሪያ ዋና ከተማ ቬይና በተካሄደው የወንዶች ማራቶንን አሸንፎ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ደራራ ሁሪሳ ተጫምቶት የነበረው የጫማ ሶል (መርገጫው) ከሚፈቀደው በላይ አንድ ሴንቲ ሜትር ወፍሮ በመገኘቱ ውጤቱ ውድቅ ተደርጎበታል።

አትሌት ደራራ ውድድሩን 2፡09፡22 በሆነ ሰዓት ቢያጠናቅቅም ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የውድድር ደንብን በመጣሱ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ተነግሮታል።

የውድድሩ አዘጋጆች አትሌቶች መጫማት የሚችሉት የጫማ ሶል ውፍረት 4 ሳንቲ ሜትር መሆን አለበት ይላሉ። አትሌቱ ግን ተጫምቶት ነበረ የተባለው የጫማ ሶል 5 ሳንቲ ሜትር የሚወፍር መሆኑን ሮይተር የዜና ወኪል የውድድሩን አዘጋጆች ጠቅሶ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም አትሌት ደራራ ከውድድሩ መጀመር በፊት በሞላው ቅጽ ላይ የተለየ ጫማ አድርጎ ወደ ውድድሩ ስለመግባቱ ተመልክቷል።

"በቴክኒክ ስብሰባ ላይ በጫማ ዙሪያ ያለውን መመሪያ ትኩረት ሰጥተን ተናግረናል። አለመታደል ሆኖ የአትሌቱን ውጤት ከመሰረዝ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረንም" በማለት የውድድሩ አስተባባሪ ሃነስ ላንገር ተናግረዋል።

"እንደዚህ አይነት ነገር ሲከሰት ይህ የመጀመሪው ነው። በውድድሮች ላይ እንደዚህ አይነት ነገር እንዳይከሰት ቀድሞ ማጣራት የሚቻልበት አሰራራ ከአሁን በኋላ ይኖራል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ የውድድሩ አዘጋጅ ተናግረዋል።

ከአትሌት ደራራ ቀጥሎ በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ኬንያዊው ሊኦናርድ ላንጋት የአንደኝነት ደረጃውን በመያዝ የውድድሩ አሸናፊ ተብሏል።

"የአትሌቱ ውጤት እንደተሰረዘ አልሰማሁም ነበር። ውድድሩን ለማሸነፍ አቅጄ ነበር። በመጨረሻ በማሸነፌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ" ብሏል ኬንያዊው አትሌት ላንጋት።

ይህ ውድድር በየዓመቱ ሚያዝያ ወር ላይ ይካሄደ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት መካሄዱ በበርካታ አትሌቶች ተቃውሞን አስተናግዶ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከፍተኛ ሙቀት ነው።

በተያያዘ ዜና እዚያው ኦስትሪያ ውስጥ በግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረ አትሌት ሕይወቱ ስለማለፉም ተሰምቷል።

የውድድሩ አዘጋጆች እንዳሉት ከሆነ፤ የ40 ዓመቱ የኦስትሪያ አትሌት ውድድሩን ከጨረሰ በኋላ ራሱ ስቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ነው ሕይወቱ ያለፈው።

የውድድሩ አዘጋጆች በክስተቱ እጅጉን ማዘናቸውን ከመግለጽ ውጪ ስለ አትሌቱ አሟሟት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።