በአረብ ኤምሬት በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መፈፀሙን አንድ ሪፖርት አመለከተ

ታትሟል

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አፍሪካውያን ስደተኛ ሠራተኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መፈፀሙን አንድ ሪፖርት አመለከተ።

ሁለት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ያወጡት ሪፖርት እንዳመለከተው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ሠራተኞች በጭካኔ ተይዘው ወደ እስር ቤት ከተወረወሩ በኋላ በግድ ወደ አገራቸው ተባረዋል።

ድርጅቶች በሠሩት በዚህ ጥናት አፍሪካውያን ስደተኛ ሠራተኞች የሚደርስባቸውን ስቃይና እንግልት በዝርዝር ተመልክተዋል።

የዩሮ- ሜዲትራኒያን ሂዩማን ራይትስ ሞኒተር እና ኢምፓክት ኢንተርናሽናል ፎር ሂማን ራይትስ ፖሊሲስ የተባሉት ሁለቱ ድርጅቶች፤ ስደተኞቹ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በጅምላ እንዴት እንደታሰሩና በእስር ቤት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መያዛቸውን ባወጡት አዲስ ሪፖርት አብራርተዋል።

ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አንዱ ኡጋንዳዊው ስደተኛ ኬኔዲ ሩባጋኬኔ ነው።

ኬኔዲ ለቢቢሲ ፎከስ ኦፍ አፍሪካ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዳ "በቀጥታ ወደ እስር ቤት ነው የወሰዱን፤ ፖሊስ ጣቢያ እንኳን አይደለም። ሁኔታው አስገርሞኝ ነበር ምክንያቱም እዚያ ለምን እንደወሰዱኝ አላወቅኩም፤ ሕጋዊ ማስረጃ ነበረኝ። የሥራ ቅጥር ውሌም ታድሶ ነበር" ብሏል።

ኬኔዲ ጨምሮም ሊከሰስበት የሚችል አንድም ወንጀል እንዳልነበር ይገልጻል። ኬኔዲ እንዳለው ፍርድ ቤትም አልቀረበም።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናት በበኩላቸው እስሩ ሕጋዊ እንደነበርና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች፣ ሥነ ምግባር በጎደላቸው ድርጊቶች እና በዘረፋ ላይ የተሳተፉ እንዲሁም የወሲብ ንግድ ሰንሰለት ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ "የታሰሩት ስደተኞችም በእነዚህ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፈዋል' ሲሉ አክለዋል።

አጥኚዎቹ ተጎጂ የሆኑና በአብዛኛው ከኡጋንዳ፣ ከካሜሩንና ከናይጀሪያ የሄዱ ከ100 በላይ ስደተኞችን አነጋግረዋል።

እነዚህ ስደተኞች ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውና በፅዳት፣ በአስተናጋጅነት፣ በነርስነትና በኤሌክትሪክ ባለሙያነት ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች ላይ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ እንደሆኑ ሪፖርቱ አመልክቷል።

ከዩሮ ሜዲትራኒያን ሂማን ራይትስ ሞኒተር በኩል አጥኚ የሆኑት ሚካኤላ ፑግሌስ "ጥቃቱ የታቀደ፣ ኢላማ ያደረገ እና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚካኤላ አክለውም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሠራተኞች መካከል ያለው መብት በዘራቸው ምክንያት እንደሚለያይም ገልጸዋል።

በዚህ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት በምላሹ ዘረኝነት በተመለከተ በሪፖርቱ የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ ያደረገ ሲሆን አገሪቷ በማንኛውም ጉዳይ ከአድልዎ የፀዳ አሠራርን በተመለከተ ጥብቅ ሕጎችንና ልምዶችን እንደተቀበለች በአፅንኦት ገልጿል።